ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል

ሠራተኞቹ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው የጦና ንቦቹ ደግሞ በሊጉ መቆየተቻውን አረጋግጠው ወደ መጨረሻው ሳምንት አምርተዋል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም 9 ሰዓት ሲል የወላይታ ድቻ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በሁለቱም በኩል ጥንቃቄ የተሞላባቸው እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ባስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ወልቂጤዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሳሙኤል አስፈሪ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የኋላሸት ሰለሞን በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ መሬቱ ላይ በማንጠር ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

\"\"

24ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ሾልኮ በመውጣት ያገኘው ብዙዓየሁ ሰይፉ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት አልፎ አልፎ በሚያገኟቸው ኳሶች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ወላይታ ድቻዎች በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 36ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። በዚህም ቃልኪዳን ዘላለም ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ወደፊት ሄዶ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ኃይል በሌለው የግንባር ኳስ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ሠራተኞቹ በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ወደፊት በመጠጋት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 44ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ሰይፉ እና ጌታነህ ከበደ ተቀባብለው ሳጥን ውስጥ ያስገቡትን ኳስ በመጨረሻም ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ ሲሞክረው ተከላካዩ ደጉ ደበበ ተደርቦ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ አጋማሹን የጀመሩት ድቻዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን ወሳኝ ዕድል አግኝተው ነበር። ቃልኪዳን ዘላለም በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በትክክል ማግኘት ያልቻሉት ቢንያም ፍቅሩ እና ያሬድ ዳዊት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በርካታ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት ወልቂጤዎች 75ኛው ደቂቃ ላይ ግብ የሚያስቆጥሩበት ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሊጠቀም የነበረው አቤል ነጋሽ ላይ ያሬድ ዳዊት ልብሱን በመጎተት በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ሲመታ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል።

መጠነኛ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ በሠራተኞቹ በኩል አቡበከር ሳኒ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ተገልብጦ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ሲወጣበት በሦስት ደቂቃ ልዩነት ደግሞ በጦና ንቦቹ በኩል ቃልኪዳን ዘላለም ያሻገረለትን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው አበባየሁ ሀጂሶ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ይዞበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ሰዓት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 በማሸነፉ ወላይታ ድቻ አለመውረዱን ሲያረጋግጥ ወልቂጤ ከተማ የመጨረሻውን የጨዋታ ሳምንት ለመጠበቅ ተገዷል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አሁንም ቢሆን ዕድሉ በራሳቸው እጅ አንደሆነ እና እንደማይወርዱም እርግጠኝ መሆናቸውን አበክረው በመግለጽ ጌታነህ ከበደ ያባከነውን የፍጹም ቅጣት ምትም ያስቆጥረዋል ብለው እርግጠኛ እንደነበሩ ሲናገሩ ከሌላው ቀናት በተለየ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ነገር እንዳሳዩ በመጠቆም ተጫዋቾቻው በቀጣዩ ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እና ላለመውረድ የሚደረገውን ትግል እናሳካዋለን ብለው እንደሚያምኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

 የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው የዛሬው ጨዋታ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት እንደነበር እና ተጫዋቾቹ ጋርም ጫና እንደነበር ጠቁመው የነበራቸው ጉጉት ከአቅማቸው በላይ እንደነበር ሲናገሩ በዝውውሩ ብዙም ሳይሳተፉ እና የውጭ ሀገር ተጫዋች ሳያካትቱ በወጣት ተጫዋቾች ላለመውረድ የሚደረገውን ትግል ስላሳኩ ደስታቸውን በመግለጽ ብዙ የሚማሩበት የውድድር ዓመት እንደነበር እና ከሳምንት በኋላ ውላቸው የሚያልቅ ቢሆንም ከክለቡ ጋር ባላቸው ነገር ደስተኛ እንደሆኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።