ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጨዋታ እየቀረው የ2015 ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቸርነት ጉግሣ እና እስማኤል ኦሮ አጎሮ ግቦች 2-0 በመርታት 29ኛ የሊግ ዋንጫቸውን አንስተዋል።

\"\"

የዋንጫውን አሸናፊ በመወሰኑ ረገድ ትልቅ ሚና የነበረው የሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ቀን 9 ሰዓት ላይ ሲደረግ በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ፈረሠኞቹ ብልጫውን ወስደዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በሞከረው እና ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በመለሰው ኳስ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ጊዮርጊሶች 20ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቸርነት ጉግሣ ከናትናኤል ዘለቀ የተሻገረውን ኳስ ከተከላካዮች ሾልኮ ወጥቶ በመቆጣጠር በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮታል።

ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅቶ ለመግባት የተቸገሩት ሀዲያዎች ይባስ ብሎም 25ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ እጅግ ተቃርበው ነበር። ቸርነት ጉግሣ በግራ መስመር ብርሃኑ በቀለን አታልሎ በማለፍ በሳጥኑ የግራ ክፍል ለገባው ረመዳን የሱፍ አቀብሎት ረመዳን ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ እጅግ ድንቅ በሆነ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ፈረሠኞቹ 49ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሄኖክ አዱኛ ከረጅም ርቀት ያሻማው እና የሀዲያ ተከላካዮች የመለሱትን ኳስ በግራ መስመር ላይ ሆኖ ያገኘው ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ሲያሻግረው ለመግጨት ጥሩ ቦታ ላይ የነበረው እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ከቀኙ የግቡ ቋሚ ጋር ተጋጭቶ ግብ እንዲሆን አድርጎታል።

የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ መፈተን ያልቻሉት ነብሮቹ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ተመስገን ብርሃኑ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን በመልሶ ማጥቃት ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። ቢኒያም በላይ በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ግብ ጠባቂውን ፔፔ ሰይዶን ማለፍ ቢችልም ከጠበበው የግቡ የግራ ቋሚ በኩል ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ብርሃኑ በቀለ መልሶታል።

መሪነታቸውን ካጠናከሩ በኋላ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ጊዮርጊሶች ከቅጣት ምት ከተደረገባቸው ሙከራ ውጪ ጨዋታውን አረጋግተው 2-0 ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ፈረሠኞች 29ኛ ዋንጫቸውን ከፍ አድርገዋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ተጋጣሚያቸው በመስመር ጥቃት የተሻለ እንደነበር በማንሳት የተከላካዮች መዘናጋትም ለጎሎች መቆጠር ምክንያት እንደነበር ጠቁመው ተጫዋቾቻችው ዓመቱን መስዕዋትነት በመክፈል ለሰጡት አገልግሎት አመስግነው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ረሰተላልፈዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው በዓመቱ ያሳዩትን ትጋት አድንቀው በዛሬው ጨዋታ የተሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ማየታቸውን በማንሳት ሁሉም ተጫዋቾቻቸው አቅም ያላቸው በመሆኑ ለወጣቶች ዕድል እንደሚሰጡ ተናግረው የምስጋና እና የእንኳን ደስ ያላችሁ ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።