ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ 16ኛ የዓመቱ ድላቸውን አሳክተዋል

ኢትዮጵያን ወክለው በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተካፋይ መሆናቸውን ያረጋገጡት ባህርዳር ከተማዎች በየአብስራ ተስፋዬ ብቸኛ ጎል ሀዋሳ ከተማን አሸንፏል።

ባህርዳር ከተማ ከሲዳማው ሽንፈት በአምስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርጓል። በዚህም ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ ቻርለስ ሪባኑ ፣ አለልኝ አዘነ እና ሀብታሙ ታደሰ አርፈው ታፔ አልዛየር ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ፉዓድ ፈረጃ ፣ ፍቅረሚካኤል አለሙ እና አደም አባስ ተተክተው ሲገቡ ሀዋሳዎች ኤሌክትሪክን ከረቱበት ስብሰባቸው ዳንኤል ደርቤን በሰይድ ሀሰን የተኩበት ብቸኛው ለውጣቸው ሆኗል።

\"\"

የሳምንቱ ማሳረጊያ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባህርዳር ከተማዎች ኳስን በመያዝ ብልጫውን ለመውሰድ ጥረት ሲያደርጉ ብንመለከትም የባህርዳርን የቅብብል ሒደት በማቋረጥ ኳስን በሚይዙበት ወቅት በሽግግር በመስመር በኩል አጋድለው ሲጫወቱ የታዩት ሀዋሳዎች የጠሩ ዕድሎችን በመፍጠሩ ሻል ያለ ቆይታ ነበራቸው። 9ኛው ደቂቃ ላይ ከዚሁ የጨዋታ መነሻቸው ሀዋሳዎች ዓሊ ሱለይማን ከግራ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ሙጂብ በግንባር ገጭቶ ታፔ አልዛየር በጥሩ ቅልጥፍና በተቆጣጠረበት አጋጣሚ ቀዳሚውን ሙከራ አድርገዋል። የጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ ባህርዳር ያመዝን እንጂ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በቶሎ ሲገቡ አደገኛ መልክን የተላበሱት ሀዋሳዎች አሁንም ሁለተኛ ሙከራን አድርገው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በአንድ ለአንድ ግንኙነት ዓሊ ኳስን በመያዝ ወደ ግብ ክልል እየገፋ ገብቶ በቀላሉ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ፈቱዲን ጀማል ከግብነት ኳሷን ታድጓታል።


በቁጥጥር ይሻሉ እንጂ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ደቂቃዎች ለመጠበቅ የተገደዱት ባህርዳሮች ፉዐድ እና የአብስራ ከቅጣት ሞክረው አላዛር ሳይቸገር ከተቆጣጠራቸው ሙከራዎቻቸው በኋላ ወደ ፊት ሳብ እያሉ በመጫወት ቀዳዳ ፍለጋ በይበልጥ ጀምረዋል። 29ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ታፔ በረጅሙ የለጋውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ከተቆጣጠራት በኋላ የግብ ጠባቂው አላዛርን መውጣት ተመልክቶ ወደ ጎል የመታት ኳስ በግቡ የላይኛው አግዳሚ ብረት ከወጣችባቸው በኋላ አጋማሹ ሊገባደድ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ቡድኑ ግብ አስቆጥሯል። 45+1ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ በአላዛር ኳሷ ስትመለስ ከተደረጉ ንክኪዎች በኋላ የአብስራ ተስፋዬ ማራኪ ጎል ከመረብ አሳርፎ አጋማሹ በጣና ሞገደኞቹ 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።


ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በብዙ ነገሮች ተቀዛቅዞ የነበረ ሲሆን የቡድኖቹ ጨዋታ ሜዳ ላይ ይደረጉ ከነበሩት ቅብብሎች ውጪ በቀላሉ ዕድሎች ተፈጥረው መመልከት ያልቻልንበት ነበር ማለት ይቻላል። ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታ ራሳቸውን በይበልጥ ለማስገባት በተደራጀ አካሄድ መጫወት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን እምብዛም የነበሩ ሲሆን የኋላ ኋላም ተከላካያቸውን በቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል ተመሳሳይ ጥፋቶችን በፍፁም ጥላሁን ላይ መስራቱን ተከትሎ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በቀይ ካርድ ሊገደድ ተገዷል። ከሚደረጉ ከእንቅስቃሴዎች ውጪ ከግብ ዕድሎች ጋር ብዙም የተራራቀው ሁለተኛው አጋማሽ 75ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳሮች በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ግልፅ የማግባት ዕድልን ቢያገኙም ተጫዋቹ ኳሷን መጠቀም ሳይችልባት ቀርቷል።


በሌላ የባህርዳር ሙከራ በጥሩ ቅብብል የአብስራ ያቀበለውን ወጣቱ ይሄነው የማታ ወደ ጎል መቶ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት እንዲሁም በተጨራረፉ ኳሶች ሲዲቤ በግንባር ገጭቶ አላዛር ካወጣበት በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግቦችን በጨዋታው ሳንመለከት በመጨረሻም በባህርዳር ከተማ የ1ለ0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ አሪፍ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው ከዕረፍት በፊት ከሌላው ጊዜ በተሻለ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው መጠቀም ባለመቻላቸው ሊሸነፉ እንደቻሉ ጠቁመው አራተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ በቀጣይ የአርባምንጭ ጨዋታን ለማሸነፍ እንደሚዘጋጁም ጭምር ተናግረዋል። የባህርዳር ከተማ አቻቸው ደግአረገ ይግዛው በአንፃሩ ጥሩ ጨዋታ ነበር ካሉ በኋላ ሀዋሳ አራተኛ ሆኖ ለመጨረስ ጠንክሮ መቅረቡን የገለፁ ሲሆን ጨዋታውን ተቆጣጥረው ማሸነፍ እንደቻሉ እንዲሁም ክለባቸው በዛሬው ዕለት ሩጫ አዘጋጅቶ ቀኑ በደስታ ተጀምሮ ነበር ካሉ በኋላ ምሽቱንም በድል አጠናቀናል ሲሉ በንግግራቸው ጠቁመዋል።