ዐፄዎቹ ውበቱ አባተን በይፋ በአሠልጣኝነት የሾሙበትን መግለጫ ሰጡ

👉\”…በሁለተኛው ዓመት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ግዴታ በውሉ ላይ ተቀምጧል\” አቶ ባዩ አቧይ

👉\”ሊጉ ላይ ካሉ አሠልጣኞች ያላነሰ ደሞዝ አገኛለሁ\” ውበቱ አባተ

👉\”ለተጫዋቾች ዝውውር የተጋነነ ጥያቄ አቅርቧል የሚባለው ውሸት ነው\” ውበቱ አባተ

👉\”ከውጤት እና ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው ደጋፊዎች ነበሩ\” አቶ አብዮት ብርሃኑ

በ2013 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከፍ አድርጎ ማንሳት የቻለው ፋሲል ከነማ በተጠናቀቀው ዓመት ወጥነት የጎደለው ውጤት በማስመዝገብ 6ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል። ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ እንቅስቃሴዎችን የጀመረ ሲሆን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩትን ውበቱ አባተን በሦስት ዓመት ውል ማስፈረሙን በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ መግለፁን ከሰዓታት በፊት ዘግበን ነበር።
\"\"
በጁፒተር ሆቴል በተከናወነው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፋሲል ከነማ ፕሬዝዳንት አቶ ባዩ አቧይ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ እንዲሁም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተገኝተዋል። በቅድሚያ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ባዩ በተጠናቀቀው ዓመት ክለቡ የነበረበትን የውጤት ዝቅታ በደንብ እንደገመገሙ በማንሳት እንደ ክለብ ለ5 ዓመታት የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድ በማቀድ ወደ እንቅስቃሴ እንደገቡ ጠቅሰው በዚህ ሂደት አሠልጣኝ ውበቱ አባተን በ3 ዓመት ውል እንዳስፈረሙ አመላክተዋል።

የአሠልጣኙ በክለቡ መሾም ከሳምንታት በፊት በሚዲያዎች ሲነገር ክለቡ ስላስተባበለበት መንገድ የተናገሩት ሥራ-አስኪያጁ አቶ አብዮት በበኩላቸው ሌላ አሠልጣኝ እያለ አዲስ ሹመት መምጣቱ እንዲሁም ውሉ በፌዴሬሽን ሳይፀድቅ ለሚዲያ መውጣቱ አግባብ ስላልሆነ እንዳስተባበሉ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ክለቡ ከቀድሞ አሠልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ ጋር በተያይዞ በተላለፈበት ክስ ታግዶ የነበረ ቢሆንም ያንን ጉዳይ ፈተው ይህንን ስምምነት እንደፈፀሙ ገልፀዋል።

\"\"

በቀጣይነት መድረኩን የተረከቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከብሔራዊ ቡድን ጫና በአንፃራዊነት ቀለል ወዳለው ስራ እንደመጡ ቢገልፁም ይሄም ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ እና ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደተዘጋጁ እንዲሁም የክለቡን ዕቅል ለማስፈፀም እንደመጡ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተናግረዋል። ከቡድን ግንባታ ጋር ተያይዞም ዲሲፕሊን የሆኑ፣ ወጣት እና ለሚፈልጉት አጨዋወት ቅርብ የሆኑ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አንስተው ከአሠልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ተያይዞ አሁን በቡድኑ ያሉት ረዳቶች እንደሚቀጥሉ እና በሌሎች ኃላፊነቶች ቡድኑን የሚረዱ ባለሙያዎችን የመጨመር እቅድ እንዳለ አክለዋል። አያይዘውም ከክለቡ ጋር ሲነጋገሩ \’ቡድኑ ምንድን ነው የሚያስፈልገው\’ የሚለውን እንዳዩ እና ቡድኑ ያለፉትን አመታት የተወሰኑ ማስተካከያዎች ብቻ እያደረገ መቀጠሉ ለውጤታማነቱ ትልቁ ነገር እንደሆነ በመተማመን ቡድን አፍርሶ መገንባት በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ስለማይቻል ባሉ ክፍተቶች ላይ ብቻ ተጫዋቾችን እንደሚያመጡ እንዲሁም ለተጫዋቾች ዝውውር የተጋነነ በጀት እንዲያዝ ጠይቀዋል የሚባለው ውሸት እንደሆነ ገልፀዋል።

በጋዜጠኞች ጥያቄ መሠረት ዳግም ንግግር ያደረጉት አቶ ባዩ በውሉ መሠረት አሠልጣኙ በመጀመሪያው ዓመት ቡድኑን የመገንባት እና በሊጉ ተፎካካሪ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። አያይዘውም በ5 ዓመቱ ዕቅድ መሠረት ክለቡ በሀገራችን ሊግ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ክለቦች መካከል አንዱ ማድረግ ግባቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

\"\"

የ2015 ላይ የነበረውን ክፍተት በዝርዝር ገምግመናል ያሉት አቶ ባዩ በተለይ የተጫዋች ዝውውር ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እንዲሁም የዲሲፕሊን እንከኖች ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። አስከትለውም ክለቡን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ በተለይ ከደጋፊዎች ጋር የተገናኙ ስራዎችን ለመስራት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

ከዚህ ከደጋፊዎች ጋር በተያያዘ አቶ አብዮት በክለቡ እና በደጋፊዎች መካከል እንደሚወራው ክፍተቶች እንደሌሉ አውስተው ከውጤት እና ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው ደጋፊዎች እንዳሉ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ችግርም በቀጣይ እንደሚሻሻል አመላክተዋል።
\"\"
በጋዜጣዊ መግለጫው በተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት በስፋት ሲጠየቅ የነበረው የአሠልጣኞኙ የደሞዝ ጉዳይን በተመለከተ ክለቡም ሆነ አሠልጣኙ ከመግለፅ ቢቆጠቡም ክለቡ በሊጉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን አሠልጣኞች ወቅታዊ ክፍያ አይቶ ሌሎች ከሚከፍሉት ባልወጣ ነገር ተነጋግሮ እንደሚከፍል ሲገለፅ አሠልጣኙም የደሞዙን መጠን መግለፅ ችግር ባይኖርባቸውም አሁን ላይ ግን መጠኑን መጥቀስ በብዙ ምክንያቶች ጥሩ ስለማይሆን አለመጥቀሱን መርጠው ሊጉ ላይ ካሉ አሠልጣኞች ያላነሰ ደሞዝ እንደሚያገኙ ጠቁመው ጥያቄውን አልፈዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እሳቸውን ለመቅጠር ሌሎች ክለቦች ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በሦስት ምክንያቶች የፋሲልን ስራ እንደተቀበሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። አንደኛው ከዚህ ቀደም በፋሲል ከነማ ሲያሰለጥኑ የደጋፊውን ስሜት እና የአመራሩን ቁርጠኝነት ማወቃቸው፣ አመራሮቹ እሳቸውን ለማምጣት ያለቸውን ፍላጎት እና ክብር ማየታቸው እንዲሁም በክለቡ ረዘም ያለ ጊዜ የሚሰሩበት መንገድ መመቻቸቱ ክለቡን ለመምረጣቸው ምክንያቶች እንደሆኑ ገልፀዋል። ከዚህ ውጪም ከብሔራዊ ቡድን እንደወጡ ሌሎች ስራዎች ቢመጡም ለራሳቸው ጊዜ መስጠትን መርጠው ቀድመው የመጡትን ጥያቄዎች ውድቅ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

\"\"

በመጨረሻ አሠልጣኝ ውበቱ እና አቶ አብዮት ስምምነታቸውን በፊርማ አፅንተው የማሊያ ርክክብ እና የፎቶ መነሳት መርሐ-ግብር ተከናውኖ መግለጫው ፍፃሜውን አግኝቷል።