ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ወደ ሊጉ የሚመለሱበትን ኃላፊነት ለማግኘት ከጫፍ ደርሰዋል

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚሳተፍ አንድ ክለብ አዲስ ኃላፊነት ለማግኘት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ ካሏት የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ዓምና ከፊፋ በመጣላቸው የኤክስፐርት ኃላፊነት ምክንያት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያላቸውን ውል በስምምነት አፍርሰው እንደነበር አይዘነጋም። ኢንስትራክተሩ ያለፉትን ወራት በሀገር ቤት እና በሀገር ውጪ የካፍ እና ፊፋ ሥራቸውን ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን አሁን ደግሞ በተጨማሪነት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሚሳተፍ አንድ ክለብ አዲስ ኃላፊነት ለማግኘት ከጫፍ መድረሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ያመላክታል።
\"\"
ኢንስትራክተር አብርሃምን ለመሾም የወሰነው ክለብ መቻል ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ያሳለፈው መቻል 40 ነጥቦችን በመያዝ 9ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል። ክለቡ ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ለመቀጠል ባለመፈለጉ ሌሎች አማራጮችን ሲመለከት የነበረ ሲሆን በደረጃ አራት አሠልጣኞችን በምርጫው አስገብቶ ነበር። ከአራቱ አሠልጣኞች ደግሞ ቀዳሚው ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ኖነዋል። ይህ ቢሆንን ግን አሠልጣኙ በቀጣዩ ዓመት እስከ የካቲት ወር የካፍ ተደራራቢ ስራዎች ስለሚኖርባቸው ክለቡን በአሠልጣኝነት ወይስ በቴክኒክ አማካሪነት ኃላፊነት እንደሚረከቡ እስካሁን አልታወቀም።
\"\"
ክለቡ እና ኢንስትራክተሩ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማየት ድርድሮችን እያደረጉ ሲገኙ ኢንስትራክተሩ በቅርቡ በአሠልጣኝነት ወይስ በቴክኒክ አማካሪነት ኃላፊነቱን ይረከባሉ የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል።