የእለቱ ዜናዎች: ጥቅምት 20 ቀን 2010

​ባምላክ ተሰማ በድጋሚ ተጠባቂ ጨዋታ ይዳኛል

ኢትዮጵዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት የሚገኙት ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ ዳካር ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲመራ ተመርጧል፡፡ ባምላክ ባሳለፍነው ሳምንት ቶታል የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አል አህሊ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ 1-1 ሲለያዩ ጨዋታውን በብቃት መምራት ችሏል፡፡ ባምላክ ከወዲሁ ሩሲያ ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫም አፍሪካን ወክለው ሊመረጡ ከሚችሉ አርቢትሮች መካከል መሆን የሚችልበት እድሉም የሰፋ ይመስላል፡፡

ከፍተኛ ሊጉ ተራዝሟል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጥቅምት 26 ሊጀመር ቢታቀድም በሁለት ሳምንት ተራዝሞ ህዳር 9 እንዲጀምር ተወስኗል፡፡ ክለቦች አመታዊ ክፍያ ከፍለው አማጠናቀቃቸው ለውድድሩ መራዘም ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡

ኃይለየሱስ ባዘዘው የአካል ብቃት ፈተናውን አለፈ 

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ትላንት ጠዋት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጠው የአካል ብቃት ፈተናን በብቃት በመወጣት ማለፍ ችሏል። ይህን ተከትሎ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ በላከው ኢንተርናሽናል ዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ የማይካተት ቢሆንም እስከ ጥር ወር ድረስ የሚመጡ አለም አቀፍ ውድድሮችን ብቻ በኢንተርናሽናል ዳኝነት ሊመራ እንደሚችል ሰምተናል።

የአካል ብቃት ፈተናውን ወድቅሀል መባሉን ተከትሎ  በግልፅ ለሚዲያው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ያለውን ያሰራር ክፍተት በመናገሩ ሊቀጣ እንደሚችል ቢነገርም የዳኞች ኮሚቴ ሀሳቡን በመናገሩ እንደማይቀጣው ማሳወቁ ይታወቃል ።

ደደቢት የአሰልጣኝ ሽግሽግ አደረገ

ደደቢት የሴቶች ቡድኑን ከ2009 የውድድር አመት በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ የወንዶች ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት እንዲሆን ወስኗል፡፡ በምትኩ ደግሞ የዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ የነበሩት ኤልያስ ኢብራሂም የሴቶች ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ የተደረገ ሲሆን ዛሬ የማሰልጠን ስራቸውን መጀመራቸውን ሰምተናል።

ኮስታዲን ፓፒች አዲስ አበባ ደርሰዋል

የኢትዮዽያ ቡና ዋና አሰልጣኝ ለመሆን የተስማሙት ኮስታዲን ፓፒች ትላንት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡  ክለቡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ የታወቀ ሲሆን አሰልጣኙም በይፋ  ቡድኑን የማሰልጠን ስራቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮዽያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እና የቡድን መሪውን አቶ ሰይፈ ዘርጋባቸው የስራ ዝውውር በሚል ከኃላፊነታቸው እንዳነሳ ታውቋል። በተጨማረም ክለቡ ሁለት የማሊ እና የኮትዲቯር ዜግነት ያላቸው የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን እንዳስመጣ ተነግሯል፡፡

የአፍሪካ ዜናዎች

ቡርኪና ፋሶ

የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ግብ ጠባቂ ሶላማ አብዱላሂ በ38 ዓመቱ በሞት ተለይቷል፡፡ አብዱላሂ ለረጅም ግዜያት የጋናዎቹን ታላላቅ ክለቦች አሻንቲ ኮቶኮ እና ሃርትስ ኦፍ ኦክ ግብ የጠበቀ ሲሆን ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በህመም ላይ ይገኝ ነበር፡፡ አብዱላሂ በ2013 ለሃገሩ አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በቡርኪና ፋሶ 4-0 ስትሸነፍ ኳስን ከሳጥኑ ውጪ በመያዙ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ በበዙዎች ይታወሳል፡፡ እሁድ እለት በተደረገው የጋና ኤምቲኤን ኤፌ ዋንጫ ፍፃሜ አሻንቲ ኮቶኮ ባላንጣው ሃርትስ ኦፍ ኦክን 3-1 ሲረታ በሁለቱም ክለቦች መለያ የተጫወተው አብዱላሂን አስበውታል፡፡

ሴራ ሊዮን

የሴራ ሊዮን እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንትነታቸው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በፍርድ ቤት ወሳኔ እስኪያገኙ የተነሱት ኢሻ ጆንሰን እና የእግርኳስ ማህበሩ ክርስቶፈር ካማራ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ መሆናቸውን እየገለፁ ሲገኝ የሴራ ሊዮን ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኢሻ ላይ የመሰተውን ክስ ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል፡፡ ዛሬ በፍሪታውን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለቱም የእግርኳስ ማህበሩ ባለስለጣናን በ65ሺ የአሜሪካ ዶላር ከእስር መፈታታቸውን ፉትቦል ሴራሊዮን ዘግቧል፡፡

የአልጄሪያ በቻን ያለመሳተፍ ጉዳይ

ሞሮኮ በምታስተናግደው የቻን ውድድር ግብፅ እሯሷን ማግለሏን ተከትሎ የካፍ ስራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ እድሉን ለምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዞን እንዲሰጥ መወሰኑን ተክተሎ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በደርሶ መልስ ጨዋታ ተገናኝተው አላፊው ወደ ቻን እንዲያመራ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይህ እድል በካፍ ደንብ ከሆነ ለአልጄሪያ የተገባ ቢሆንም የሞሮኮ በካፍ ያላት ተሰሚነት መግዘፍ አልጄሪያ ከቻን ዋንጫ ውጪ እንዳደረጋት የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን የሰጠው አልጄሪያዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ ዋሊድ ባይልካ መሰረት የሌለው የፈጠራ ወሬ ሲል መረጃዎቹን አጠጥሏል፡፡ ከሴሜን አፍሪካ ዞን ሁለት ሃገራት (ሞሮኮ እና ሊቢያ) እንደመሳተፋቸው ለዞኑ የተሰጠው ቦታም ሁለት እንደመሆኑ የሞሮኮ ተፅዕኖ በካፍ ማየል ለአልጄሪያ አለመሳተፍ እንደምክንያት ያቀረቡ ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸው ሲልም ባይልካ ሃሳቡን አክሏል፡፡

ግብፅ

ታዋቂው የቡርኪና ፋሶ አጥቂ አሪስቲድ ባንሴ ክለቡ አል መስሪ ወርሃዊ ክፍያውን በወቅቱ ባለመክፈሉ ከግብፅ ወደ ሳውዲ አረቢያ ማምራቱን ኪንፉት ዘግቧል፡፡ ባንሴ በዓመቱ መጀመሪያ የኮትዲቯሩን አሴክ ሚሞሳስን ለቆ ወደ ፖርት ሳዒዱ ክለብ ከተዛወረ በኃላ ሶስት የሊግ ግቦች ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡ ለወራት ደሞዝ ስላልተከፈለውም ቁመተ ልግላጋው አጥቂ ወደ ሳውዲው ክለብ አል ራድ ሳያመራ እንዳልቀረ ተነግሯል፡፡ የግብፅ ክለቦች ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የሚመጡ ተጫዋቾች ጋር በደሞዝ እና በውል ምክንያት በሚፈጥሩት ውዝግብ መሰል ተመሳሳይ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ይስተዋላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *