ከድሉ በኋላ የጣና ሞገዶቹ አሠልጣኝ ምን አሉ?

የባህር ዳር ከተማው ዋና አሠልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው ቡድናቸው አዛምን 2ለ1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው

በማሸነፋችን በጣም ተደስቻለሁ። በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር ካሳለፍነው ነገር አንፃር ከውጤቱም ባለፈ ሜዳ ላይ መገኘታችን በጣም ያስደስተኛል። ለጨዋታው አጭር የዝግጅት ጊዜ ነው የነበረን በተጨማሪም ተጫዋቾች ከነበርንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው በስነልቦናው ረገድ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ጥሩ የሚባል ነው።አዛም ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን ለዚህም ጨዋታ ከአንድ ወር አስቀድመው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል አራት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገው ነው ለዛሬው ጨዋታ የመጡት በአንፃሩ እኛ ከልምምድ ነው ቀጥታ ወደ ጨዋታ የገባነው በጨዋታው ኳሱ ይዘን ጉልበታችንን ቆጥበን ለመጫወት ሞክረናል።ነገርግን በሜዳው ሦስተኛ ክፍል ላይ ከፍተኛ መቻኮሎች ነበሩ ይህም የኳስ ቁጥጥራችን ይበልጥ ወደ ውጤት መቀየር ሳንችል ቀርተናል።ይህን ጨዋታ በድል መወጣታችን ለተጫዋቾቻችን በስነልቦና ረገድ ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል በጥቅሉ ግን የዛሬው ድል ይገባናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ተዳክሞ ስለመቅረቡ

በሁለተኛው አጋማሽ ሜዳ ላይ የምንፈልገውን ፍጥነት ማግኘት አልቻልንም። ከነበረን አጭር የልምምድ ጊዜ አንፃር እንዲሁም ተጫዋቾቻችን ከዕረፍት እንደመምጣታቸው በዚህ ደረጃ ለዘጠና ደቂቃ ተጫውተው ውጤት ይዘው መውጣታቸው እንደውም ሊያስመሰግናቸው ይገባል።ሜዳ ላይ እንዳየነው የአካል ብቃት ደረጃችን ገና ስራ ይፈልጋል።ከዚህ ባለፈ በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን እጅግ ሀይልን የቀላቀለ አቀራረብን መምረጣቸው ገና ችግር ጋር ተዳምሮ ፈታኝ አድርጎብናል።

በመልሶ ጨዋታ ስለሚጠብቃቸው የቤት ስራ

ለመልሶ ጨዋታ ይረዳን ዘንድ ዛሬ የተጠቀምናቸውን ተጫዋቾች ዕረፍት በመስጠት በነገው ዕለት ከሱዳን ቡድን አጋር የወዳጅነት ጨዋታ ይኖረናል በዚህም ዛሬ ያልተጠቀምንባቸውን ልጆችን ወደ ጨዋታ ዝግጁነት ለማምጣት እንጠቀምበታለን ብለን እናስባለን።እንደ ቡድን በመልሶ ጨዋታ ውጤት ይዘን ለመውጣት ያለንን የመጨረሻ አቅም ሰጥተን እንጫወታለን።መታወቅ ያለበት የዛሬው ጨዋታ እንደ ቡድን የመጀመሪያ አህጉራዊ ጨዋታችን ነው ምናልባት አግዞናል ብዬ የማስበው የተወሰኑ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ሆነ በክለብ ደረጃ በዚህ ደረጃ የመጫወት ልምዱ ነበራቸው ቢሆንም ግን በዚህ አይነት ታሪካዊ ጨዋታ ከደጋፊዎቹ ርቀህ በዝግ ያለበቂ ዝግጅት መጫወት በጣም ፈታኝ ነው።እንደ ሀገር የተቀበልነውን ይህ አደራ ለመወጣት የተቻለንን እንጥራለን ረጅም ርቀትም ብንጓዝ በጣም ደስ ይለኛል።

ስለተጋጣሚያቸው አዛም

ባየናቸው የተወሰኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሃይልን ቀላቅሎ የሚጫወት በመስመሮች ለማጥቃት የሚሞክር እንዲሁም ከአማካይ በሚደረጉ የዘገዩ ሩጫዎች ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ስለመሆኑ ያገኘናቸው የሁለት ጨዋታ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ያሳያሉ።ከዚህ አንፃር ከተከላካዮች ጀርባ ኳሶችን እንዳይጥሉ እና በመስመሮች በኩል በነፃነት እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ሞክረናል በመሰረታዊነት ግን ለማድረግ የሞከርነው በራሳችን አቅም ምን ማድረግ እንችላለን የሚለው ላይ ነበር።በግሌ ምናልባት የአየር ሁኔታው ሊሆን ይችላል ነገርግን አዛምን በጠበቁት ልክ አላገኘሁትም ከዛ ውጭ የረጃጅም ኳሶች አጠቃቀማቸው ለሁለተኛው ጨዋታ ዝግጅታችን ፍንጭ የሚሰጠን ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለአዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ

በክረምቱ አዳዲስ ተጫዋቾች አምጥተናል ምናልባት እንደ በጎ ጎን የምወስደው ያመጣናቸው ተጫዋቾች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክለቦች አብረው መጫወት የቻሉ መሆናቸው ለመግባባት የተወሰኑ ስራዎችን አቅሎልናል።

ከተጫዋቾች ቅያሬ ጋር በተያያዘ

ተጫዋቾቻችን ያሉበትን የአካል ብቃት ደረጃ ስለምናውቅ ቅያሬዎቹን በአግባቡ ለመጠቀም ሞክረናል።ቸርነትም ሆነ ሀብታሙ በሙሉ አካል ብቃት ሲገኙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ እናውቃለን በዛሬውም ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ከጠበቅነው በላይ አግዘውናል።በሁለተኛው አጋማሽ ያደረግናቸው ቅያሬዎች በተለይም በማጥቃቱ አዳዲስ ጉልበት ያላቸው ልጆችን ወደ ሜዳ በማስገባት የሚያስፈልገንን ጎል ለማግኘት ሞክረናል ነገርግን በአሰብነው ልክ ውጤታማ አልነበርንም።

ያለደጋፊ ስለመጫወታቸው

እጅግ ያስቆጫል።ይህን አይነት ጨዋታ ደጋፊዎች ቢያዩ ከተማችን ላይ ብንጫወት ከተማችን ላይ የሚኖረውን ድባብ ማሰብ የሚቻል ነው።ይህ ቢሆን ኖሮ በጣም ደስ ይለን ነበር።ከፋይናንስ አንፃር ወጪ ከማስቀረት ባለፈ በደጋፊያችን ብንታጀብ በተለያዩ መንገዶች ክለባችን ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መፍጠር ይቻል ነበር።እዚህ እንዳለመታደል ያለደጋፊ ለመጫወት ተገደናል ቢሆንም ግን ይህን ውጤት ጨዋታውን በጉጉት ይጠብቁ ለነበሩ ደጋፊዎቻችን
የሚገባ ነው።