ወልቂጤ ከተማ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ወልቂጤ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሀዋሳ ያደርጋል።

የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ባስመዘገበው ውጤት በፕሪምየር ሊጉ መክረሙን ያረጋገጠው ወልቂጤ ከተማ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ካለፈው ዓመት በተሻለ ሆኖ ለመጨረስ የአደረጃጀት ለውጥን አድርጎ በመቀጠል ወጣቱን አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን በአሰልጣኝነት ከቀጠረ በኋላ በይፋ የአስር ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የሁለት ነባሮችን ውልም እንዳራዘመ ይታወሳል። መሳይ አያኖ ፣ መሳይ ፓውሎስ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አሜ መሐመድ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ራምኬል ሎክ እና ጋዲሳ መብራቴን በይፋ አዳዲስ ፈራሚዎቹ ያደረገው ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናት የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ጨምሮ የነባሮችን ውል ከማራዘሙ አስቀድሞ ወደ ቅድመ ዝግጅት የሚገባበትን ቀን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት የፊታችን ቅዳሜ ነሀሴ 20 የክለቡ ሁሉም ተጫዋቾች በሀዋሳ ሐሮኒ ሆቴል ማረፊያቸው ካደረጉ በኋላ በማግስቱ ዕሁድ ዝግጅታቸው በከተማው ላይ መከወን እንደሚጀምሩ ታውቋል።