ከግብፅ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

👉 “ለአንዱ አሰልጣኝ ኮከብ የሆነ ለእኔ ኮከብ ላይሆን ይችላል

👉 “የእኔን ቆይታ በውጤት ላይ የተመሰረተ አይደለም

👉 “የእኛ ጉዳዩ ሞ ሳላህ ገባ አልገባም አይደለም

👉 “ከቢንያም ጋር አንድም ያልተገባ የቃላት ልውውጥ የለም

በመግቢያ ንግግር በማድረግ ስለዝግጅታቸው አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር ሁኔታዎችን የተናገሩት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ለተጫዋቾች ጥሪ ከተደረገ በኋላ የመጀመርያ ቀነ የጂም ስራ እንደጀመሩ ማስከተል እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የሜዳ ላይ ተግባራትን ሲከውኑ መቆየታቸውን ገልፀው። ከልምምዱ በተጓዳኝ የግብፅ ጨዋታን አስመልክተው ከተጫዋቾቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሁሉም በአካላዊ ጥንካሬም ሆነ በስነ ልቦናው ረገድ የተሻሉ መሆናቸውን አውስተው አበቡበከር ናስር ለመጥራት ቢታሰብም በጉዳት ላይ በመሆኑ በጥሪ ውስጥ አለመካተቱ፣ ምኞት ደበበ ጥሪ ከተደረገለት በኋላ ወባ እንደያዘው የህክምና ማስረጃ በማቅረቡ በእርሱ ምትክ ሰው እንደተካ እንዲሁም ያሬድ ባዬ በካርድ ምክንያት ካፍ በዚህ ጨዋታ ላይ ማረፍ እንዳለበት በመገለፁ በስብስብ ውስጥ አለመካተቱን፣ ቢንያም በላይ የብሽሽት ህመም አጋጥሞኛል በማለት እረፍት በመጠየቁ እርሱንም መሸኘታቸውን አብራርተዋል። በአጠቃላይ ለግብፅ ጨዋታ በሜዳም፣ በክፍል ውስጥም ሊያጋጥሙን በሚችሉ ጉዳዮች ዙርያ ስራዎችን በሚገባ ሰርተው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። በማስከተል ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ዋና ዋና በሚባሉ ጥያቄዎችንና የአሰልጣኙን ምላሾች እንዲህ አቅርበነዋል።

ስለአለልኝ አዘነ በምርጫ ውስጥ አለመካተት ?

የተጫዋቾች ምርጫን በተመለከተ ለአንዱ አሰልጣኝ ኮከብ የሆነ ለእኔ ኮከብ ላይሆን ይችላል። አንድ አሰልጣኝ ለሚጫወተው ጨዋታ ሌላውን አሰልጣኝን ተመሳሳይ ማድረግ ይከብዳል። ነገር ግን ወደ ተጫዋች ምርጫ እውነታ ስንሄድ ለምንፈልገው ማለትም ሁለት አንድ ዓይናት ነገሮችን አንመርጥም። ሁለት የለተያዩ ነገሮችን እንመርጣለን እንጂ። ለመጀመርያ ዕቅድ ማን ያስፈልጋል ለሁለተኛ ዕቅድ ማን ያስፈልጋል የሚለውን ባየነው እና ባሰብነው ልክ ጋቶች ፓኖምን እና አማኑኤል ዮሐንስ በቦታቸው የተሻሉ በመሆናቸው መመረጥ ችለዋል። ዞሮ ዞሮ አንድ አሰልጣኝ ለሚፈልገው ጨዋታ ግብአት ይሆኑኛል ብሎ የሚያስበውን ተጫዋች ይመርጣል።

በአሰልጣኝ ዳንኤል ቆይታ ዙርያ…

የእኔን ቆይታ በውጤት ላይ የተመሰረተ አይደለም። አንድ የቴክኒክ ዳሬክተር በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በሌለበት ሰአት ተክቶ ስለሚሰራ ሁለተኛ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አዲስ አሰልጣኝ ለማምጣት ጊዜው አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም በክለብ ውል ያላቸው አሰልጣኞች በመኖራቸውን ፊፋ ባስቀመጠለት ነገር ታሳቢ በማድረግ የቴክኒክ ዳሬክተሩ በጊዜያዊነት ቀሪ ጨዋታዎቹን እንዲሸፍን እንጂ ከውጤት ጋር ተያይዞ ዳንኤል ይቀጥላል አይቀጥልም የሚል ነገር ስለሌለ የእኔ ትልቁ ኃላፊነት የግብፅን ጨዋታ ጨርሶ በቀጣይ ለፌዴሬሽኑ መደላደል ማመቻቸት ስለሆነ በዚህ ቢታይ መልካም ነው።

ቢንያም በላይ በተመለከተ የተፈጠረ ሰጣ ገባ አለ…?

በዚህ ዙርያ ከቢንያም በላይ በስተቀር ታማኝ ምንጭ የለም። ከቢንያም ጋር አንድም ያልተጋባ የቃላት ልውውጥ የለም። ሰዎች የተለያዩ ነገሮች ሊያነሱ ይችላሉ። ህመም እንዳለበት ለእኔ ብቻ አይደለም የነገርው ለግብጠባቂ አሰልጣኙ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኙም ባሉበት ብሽሽቴን ስላመመኝ ወደ ቤቴ መመለስ እፈልጋለው ስላለ ህመም እያለበት ስብስብ ውስጥ መቀላቀል ኢትዮጵያ ሌላ ተጫዋቾች እንደሌሏት ስለሚመስል ፍቃድ ስለጠየቀ እንዲሄድ አድርገናል። ከዚህ ውጭ በሜዳም ከሜዳም ውጭ ከቢንያም ጋር ጤናማ ግኑኝነት አለን። ምንም አይነት የተፈጠረ ውዝግብ የለም።

ከታሪካዊ ባላንጣ ግብፅ ጋር ስለሚደረገው ጨዋታ እና የሞ ሳላህ አለመኖር…

ከታሪክ አንፃር ከልጆቹ ጋር ቁጭ ብለን ተወያይተናል። ዞሮ ዞሮ የእኛ ጉዳይ ሞ ሳላህ ገባ አልገባም አይደለም። የእኛ ትኩረት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ሸነበረን መሸነፍ በምን መልኩ የተሻለ ነገር ማድረግ እንዳለብን በውይይታችን ላይ ተነጋግረናል። ከዚህ በፊት ከእኛ ጋር የሚጫወቱ ቡድኑኖች አሳንሰው የመግባት ነገር ነበር። አሁን ግን ያ አለመሆኑን መሸነፍ እንኳን ቢኖር በጠባብ እና ከአቅም በላይ ተቸግሮ እንደሆነ እራሳቸውን ቁጭ አድርገው ተነጋግረው። ከዚህ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንደሚሰጠው አነስተኛ ግምት ሳይሆን እንደ መጀመርያው ግብፅን ማሸነፍ እንደቻሉት አሁንም ይህን እንደሚፈልጉ፣ አሻራቸውን ማስቀመጥ እንደሚፈልጉ እና ይህ ጨዋታ በዓለም ዋንጫ አንድ ምድብ ስለሆንን ለዛም ጨዋታ የቤት ስራ ሰጥቶ ለመምጣት እንዲሁም የሚጎለውን ድክመቶች ካሉ ለዓለም ዋንጫው ጨዋታ ለማስተካከል ታሳቢ ያደረገ ጨዋታ ነው። በስነ ልቦናው ረገድ በቂ ዝግጅት አድርገናል። አንድ ነገር መታሰብ ያለበት ግብፅ ስለሆነች የተለየ ዝግጅት እያደረግን አይደለም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል። ያን አልን ማለት ተጫዋቾችን በስነ ልቦና ጫና ውስጥ መክተት ነው። ስለዚህ ለማንኛውም ብሔራዊ ቡድን ስንጫወት የነበረውን የታክቲክ እና የስነ ልቦና ዝግጅት ነው ስናደርግ የነበረው።


የአማኑኤል ዮሐንስ ጉዳት በተመለከተ…

አማኑኤል ስራ ሰርቷል። መጠነኛ የሆነች የባት ህመም አጋጥሞታል። እርሱንም የማገገገም ስራ እየተሰራ ነው ያለው። አንድ ልምምድ ላይ አርፏል። ዛሬ ግን ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርቷል። ነገም እዛም አርፎ ልምምድ ይሰራል። እንጂ ምንም አይነት ችግር ይኖራል ብለን አናስብም። አማኑኤል በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ልጆቻችን በየትኛውም ቦታ አቀያይረን ማጫወት እንችላልን። ተጫዋቾቹም ይህን ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ያቁታል።