የትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን ለክልሉ ክለቦች መመርያ አስተላልፏል

የትግራይ ክልል ክለቦች ዘንድሮ ወደ ውድድር የሚመለሱበት አኳኋን ታውቋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ላለፉት ዓመታት ከሀገራዊ ውድድሮች ርቀው የቆዩት የትግራይ ክልል ክለቦች በአዲሱ የውድድር ዓመት አንድ ደረጃ ወርደው እንዲሳተፉ መወሰኑ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም የክልሉ እግርኳስ ፌደሬሽን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ክለቦች ውሳኔውን ተቃውመዋል። ሆኖም ውሳኔውን ከመቃወም ውጪ አቋማቸውን በይፋ ሳይገልፁ ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎም መቐለ 70 እንደርታ ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ በከፍተኛ ሊጉ የመሳትፋቸው ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ ቆይቷል ። አሁን ባገኘነው መረጃ ግን ትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን በክልሉ የሚገኙ በሁሉም የሊግ እርከን የሚሳተፉ ክለቦች ወደ ሀገራዊ ውድድሮች እንዲመለሱ ወስኗል።

በጉዳዩ ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበራቸው የትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ተፈራ ክለቦቹ ወደ ሀገራዊ ውድድሮች እንዲመለሱ መመርያ ማውረዳቸውን አረጋግጠውልናል። ኃላፊው በሰጡት ሀሳብም ” ክለቦቹ የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት እንዲመዘገቡ ገልፀንላቸዋል። ይህ ማለት ግን ከዚህ ቀደም ክለቦቹ ወደ ነበሩበት ሊግ መመለስ አለባቸው ብለን ያቀረብነው ቅሬታ ትተነዋል ማለት አይደለም። ጥያቄው ጎን ጎን እናስኬደዋለን” ብለዋል።