ሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ አስፈርሟል

ለዘንድሮ የውድድር ዓመት በርከት ያሉ ዝውውሮችን የፈፀመው ሲዳማ ቡና የሁለት ነባር ተጫዋቾቹን ውል በማራዘም አንድ ግብ ጠባቂ አስፈርሟል።

ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ይረዳው ዘንድ በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር  ወደ ግማሽ ፍፃሜው የተቀላቀለው ሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂው መስፍን ሙዜን ሲያስፈርም የሁለት ተከላካይ እና አማካይ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል።

በሀዋሳ ተስፋ ቡድን የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው እና በወልድያ ፣ በኢኮስኮ ፣ በባቱ ከተማ የተጫወተው ወጣቱ ግብ ጠባቂ መስፍን ሙዜ ባሳለፍነው ዓመት ዓመት ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ለሁለት ዓመት ለመጫወት ለሲዳማ ቡና መፈረሙ ታውቋል።

በሌላ በኩል የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው መሀሪ መና ያለፉትን ሁለት ዓመታት በክለቡ የቆየ ሲሆን ለተጫማሪ አንድ ዓመት በሲዳማ ለመቆየት ችሏል።

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው አበባየሁ ዮሐንስ ሲሆን ከደቡብ ፖሊስ እግርኳስን ከጀመረ በኋላ በስልጤ ወራቤ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ወደ ቀድሞው ክለቡ ሲዳማ ቡና ተመልሶ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ያሳለፈው አማካዩ ለቀጣዩ ሁለት ዓመት በሲዳማ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።