ሉሲዎቹ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል

በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ አንደኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ብሩንዲ እና ኢትዮጵያ 1-1 ተለያይተዋል።

በ2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዛሬ 09:00 ላይ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ብሩንዲ እና ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ተገናኝተዋል። ቀዝቃዛ በነበረው እና የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የጨዋታው መጀመሪያ አጋማሽ ረድዔት አስረሳኸኝ 39ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ ኢትዮጵያን መሪ ብታደርግም የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ግን ሌላኛዋ የቡድን አጋሯ ሴናፍ ዋቁማ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 48ኛው ደቂቃ ላይ ሉሲዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሎዛ አበራ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ወደ ግብ የሞከረችው አረጋሽ ካልሳ ኳሱ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶባታል። ሆኖም በአንድ ደቂቃ ልዩነት  ካንያሙኔዛ ኤሪካ ግብ አስቆጥራ ብሩንዲን አቻ ማድረግ ችላለች።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ተጫዋቾች የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። በተለይም 58ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ 61ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሎዛ አበራ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝተው ያባከኑበት አጋጣሚ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥርም ጨዋታው ይበልጥ እየተቀዛቀዘ ሄዶ 1-1 ተጠናቋል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በመጪው ማክሰኞ መስከረም 15 አበበ ቢቂላ ስታዲየም የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።