ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ጣፋጭ ድል ተጎናጽፏል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ተከታትለው ያጠናቀቁትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በአምስት ግቦች ፌሽታ ታጅቦ በመድን 3-2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ኢትዮጵያ መድን ሦስት ባህርዳር ከተማ በበኩሉ ስድስት አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን በቋሚ አሰላለፍ በተጠቀሙበት ጨዋታ ጎል ያስመለከተን ገና 4ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ሐቢብ ከማል መሐል ሜዳ ላይ ያገኘውን ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን አጠገብ ደርሶ ያመለጠችውን ኳስ ሳለአምላክ ተገኝ ከራሱ ሜዳ ለማፅዳት በሚጥርበት ወቅት ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ አሚር ሙደሲር እግር ስር ደርሳ አማካዩ ሳጥኑ ጠርዝ ያገኛትን ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ በመምታት አላዛር መረብ ላይ አሳርፏት መድንን መሪ አድርጓል። ቀጣዮቹን 20 ደቂቃዎች በመስመሮች በኩል በሚደረጉ ፈጠን ያሉ ሽግግሮች የጨዋታ መንገዳቸውን በማድረግ ሁለቱም ቡድኖች በተጫወቱበት ቀሪዎቹ ሰዓታት ባህርዳሮች ከቆመ ኳስ አቻ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል።

15ኛው ደቂቃ ላይ በመድኖች የግብ ክልል ወደ ግራ በተወሰነ መልኩ ካዘነበለ ቦታ ላይ የተገኘን የቅጣት ምት ፍሬው ሠለሞን ከተካላካዮች ጀርባ ሲያሻማ የተጫዋቾችን የቦታ አያያዝ ስህተት በአግባቡ ተጠቅሞ ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶ የጣናው ሞገዶቹን ወደ አቻነት መልሷል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በተወሰነ መልኩ በጥልቀት ወደ መሐል ሜዳ አመዝነው ለመንቀሳቀስ የጣሩት መድኖች በአቡበከር ፣ ሐቢብ እና ያሬድ አማካኝነት ክፍት ቦታ ፍለጋን በድግግሞሽ ማድረግ ቢችሉም በውሳኔ ልልነታቸው በቀላሉ የተገኙ ዕድሎች እንዲባክኑ ሆነዋል። በአንጻሩ ባህርዳሮች ኳስ ሲይዙ የተጋጣሚን የመከላከል አጥር ሰብሮ በመግባት ክፍተቶችን ለማግኘት ታትረዋል። በዚህም ሒደት 36ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሠለሞን ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ገጭቶ ኳሷ በግቡ ቋሚ ታካ ወጥታለች። ጨዋታውም በ1ለ1 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ መድኖች በአቡበከር ወንድሙ ቦታ ብሩክ ሙሉጌታን በመተካት የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ ጨዋታው ቀጥሏል። ፈጠን ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለማየት ያስቻለን ጨዋታው 46ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ ከግብ ጠባቂው አላዛር ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ አላዛር በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ክልል በቀላሉ በመድረስ ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረቶች ያልተለያቸው ባህርዳር ከተማዎች ሀብታሙ ታደሰ ካመከናት ግልፅ ሙከራ በኋላ ወደ መሪነት የመጡበትን ጎል አሳክተዋል።

52ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ከያሬድ የደረሰው ሰንጣቂ ኳስ ለፍፁም በሚያቀብልበት ወቅት አዲስ ተስፋዬ ሳጥን ውስጥ ፍፁም ላይ ጥፋት በመስራቱ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ያሬድ ባዬ አስቆጥሯታል። ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት መድኖች ከሦስት ደቂቃ መልስ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል ። ሳላአምላክ ተገኝ ሐቢብ ከማል ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት በመስራቱ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ሐቢብ አስቆጥሮት ቡድኑን ሁለት አቻ አድርጎታል።

ከ70 ደቂቃዎች በኋላ ማጥቃቱ ላይ ኃይል ለመጨመር ባህርዳሮች ዱሬሳ እና አደምን ወደ ሜዳ ቢያስገቡም መድኖች በተሻለ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ሜዳ ላይ አሳልፈዋል። ለዚህ ማሳያ ያሬድ ካገኛቸው ዕድሎች በተጨማሪ 78ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወደ ውስጥ አሻምቶ ወገኔ በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እና አሁንም ወገኔ ከሳጥን ውጪ መትቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራ ተጠቃሾቹ ናቸው። 85ኛው ደቂቃ ላይ በባህርዳር በኩል የአብሥራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት አቡበከር ሲመልስው አጠገቡ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ ነፃ ቦታ ሆኖ ዳግም ቢያገኝም ሳይጠቅምበት ቀርቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ መድኖች በፈጣን መልሶ ማጥቃት 87ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከቀኝ ወደ ውስጥ ለአሸብር ደረጄ ሰጥቶት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተጫዋቹ ግብ በማድረግ በመጨረሻም ጨዋታው በመድን 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በጨዋታው የተገኙ ዕድሎችን መጠቀም አለመቻላቸውን እና ይህም የተከሰተው ችግር እንደ ቡድን መሆኑን ገልፀው በቀላሉ የማግባት ዕድሎችን አግኝተው ማሸነፍ የሚችሉበት መንገድ እንደነበር አክለውም የተገኙትን ዕድሎችን ያለ መጠቀም ችግር ተጋጣሚያቸውን እንዲያነሳሳው እንዳደረገ በቡድናቸው ተጫዋቾችም ላይ ከጨዋታ መደራረብ አንጻር ድካም መኖሩን ከተናገሩ በኋላ ውጤቱ የማንቂያ ደወል እንደሆነላቸው አመላክተዋል። የመድኑ አቻቸው ገብረመድኅን ኃይሌ ሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች ከባድ እና ጠንካራ ስለመሆናቸው እንዲሁም የማይቆም ደስ የሚል እንደነበር ጠቁመው ወጣት ተጫዋቾቻቸው ሜዳ ላይ ሲያደርጉት በነበረው እንቅስቃሴ ስለ መደሰታቸው ተናግረዋል።