ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ዓመቱን በድል ጀምረዋል

የዓምና ሻምፒዮኖቹ ጊዮርጊሶች ወልቂጤ ላይ አራት ግቦች በማስቆጠር ድል ተጎናፅፈዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ፈረሰኞቹ በአንፃራዊነት ከተጋጣምያቸው በተሻለ መንገድ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የጠራ የግብ ዕድሎች ባልፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ በተገኑ ተሾመ ወልቂጤዎች ደግሞ በስንታየሁ መንግስቱ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በተለይም ስንታየሁ የተሻገረችለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ ቡድኑ ካደረጋቸው ሙከራዎች የተሻለች ነበረች።


በሀያኛው ደቂቃ ላይም ሄኖክ አዱኛ በወልቂጤ ሳጥን ግራ ክንፍ አካባቢ የተገኘችውን የቆመች ኳስ አሻምቷት በግቡ አፋፍ ላይ የነበረው ዳንኤል ደምሱ ራሱ ግብ ላይ በማስቆጠሩ ፈረሰኞቹ ጨዋታውን መምራት ችለዋል። በጨዋታው አንዳንድ አጋጣሚዎች ኳሱን ከመቆጣጠር ውጭ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው የነበሩት ሰራተኞቹ ጊዮርጊሶች በኳስ አመሰራረት ሂደት የሚፈጥሯቸውን ስህተቶች ሳይጠቀሙ ከቆዩ በኋላ በሰላሣ አንደኛው ደቂቃ ላይ በተጠቀሰው ስህተት የተገኘችውን ኳስ ተጠቅመው በስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አጥቂው የግዮርጊስ ተከላካይ በኳስ አመሰራረት ሂደት ከተሳሳቱ በኋላ በግንባር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነበር ግቧን ያስቆጠረው።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ መልክ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች በሁሉም ረገድ ብልጫ ወስደው በርካታ ዕድሎች ሲፈጥሩ ወልቂጤዎች ደግሞ ከመጀመርያው አጋማሽ ብቃታቸው ወርደው የታዩበት ነበር።


ሄኖክ ከአማኑኤል የተቀበለውን ኳስ ባደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ፈረሰኞቹ በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች አጥቅተው በመጫወት በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም አቤል ያለው በረዥሙ የተሻገረችለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ የቆዩት ጊዮርጊሶች በሀምሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ግን በአማኑኤል አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ጠርዝ ላይ ሆኖ አሻምቷት ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በአግባቡ ያልተቆጣጠራትን ኳስ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው። ሂደቱም የግብ ጠባቂው ጉልህ ስህተት የታከለበት ነበር። በሰባ አራተኛው ደቂቃ ላይም አቤል ያለው በወልቂጤ ሳጥን ቀኝ ጠርዝ አከባቢ የተገኘችውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልቂጤዎች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም አሜ መሐመድ በሁለት አጋጣሚዎች ሙከራ ማድረግ ችሏል። በተለይም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።


በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በርካታ ቅያሬዎች ያደረጉት ፈረሰኞቹ በሰማንያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ በተገኑ ተሾመ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው የጎል መጠናቸው ወደ አራት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ተቀይሮ የገባው አሮን በመልሶ ማጥቃት ያገኛትን ኳስ ገፍቶ ለበረከት አቀብሎት አማካዩ ዘግይቶ ወደ ሳጥን ለገባው ተገኑ ካሻገረለት በኋላ ተጫዋቹ ወደ ግብነት ቀይሯታል።

ፈረሰኞቹ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ አራት ግቦች አስቆጥረው ካሸነፉ በኋላ ሃሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ዘሪሁን ቡድናቸው በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልተንቀሳቀሰ ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተሽለው እንደቀረቡ ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ወጣት ተጫዋቾቻቸው ጥሩ እንደተንቀሳቀሱ አንስተዋል።

በመጀመርያ ጨዋታው ሽንፈት የገጠመው አሰልጣኝ ሙልጌታ በበኩሉ ጨዋታው ሁለት መልክ እንደነበረው ከጠቀሰ በኋላ የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበር ተናግሯል። አሰልጣኙ በቀጣይ የታዩባቸውን ጥቃቅን ስህተቶች አርመው ለመመለስ እንደሚጥሩ ከገለፁ በኋላ ከውጭ አዳዲስ ተጫዋቾች እንደሚያስፈርሙ ፍንጭ ሰጥተዋል።