የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 ሀድያ ሆሳዕና

“በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድሎችን በመፍጠርም የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለሁ” አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ንግድ ባንክ

“ካለማስቆጠር በስተቀር የሚገባንን አድርገናል” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – ሀድያ ሆሳዕና

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀድያ ሆሳዕናው ተጫዋች ከድር ኩሉባሊ በራስ ላይ በተቆጠረ ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ከቻለበት የምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው በጣም ጠንካራ እንደሚሆን መጀመሪያውን አውቀነው ነበር ፣ ምክንያቱም ከዚህ በፊት በደንብ አይተናቸዋል። ሲቲ ካፕም ተገናኝተናል የወዳጅነት ጨዋታን አብረን ተጫውተናል። በጣም ታክቲካል እና ወደ ኋላ አፈግፍጎ ፕረስ እያደረጉ በመልሶ ማጥቃት የሚጫወት ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ እንደሆኑ ከዚህ በፊትም አይተናቸዋል እና በደንብ ተዘጋጅተን ትኩረታችንን ሳናባክን የምናገኘውን ክፍተት መጠቀም እና ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር ያሰብነው። መጥፎ አይደለንም በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድሎችንም በመፍጠርም የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለሁ። ባሰብነው ልክ ባናገኝም ይሄ የቡድኑ ባህሪ ነው። በጣም በጥልቀት የሚከላከል ከመሆኑ አንፃር ምን አልባት በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ብዙ ዕድሎች ፣ ይሄ ክፍት ጨዋታ እንዳልሆነ እናውቃለን ከዛ አንፃር መጥፎ አይደለም። በጣም ተጭነን ተጫወትን መጨረሻ ላይ ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ደግሞ የበለጠ እንደ አዲስ ቡድን ከታች እንዳደገ በአጠቃላይም ለሊጉ አዲስ የሆኑ ልጆች እና ከታች እንደመጡ ልጆች ገና ነው ቡድናችን ፣ መጥፎ አይደለም በሂደት መስተካከል ያለበትን እናስተካክላለን ጥሩ ጨዋታ ነበር ብዬ አስባለሁ”።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው…

“ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ በሁለታችንም በኩል አንዳንድ ያገኘነውን ዕድል አልተጠቀምንም። በጊዜ ያገኘኸውን ካልተጠቀምክ ዋጋ ትከፍላለህ ስህተት ሰራን ራሳችን ላይ አገባን ሌላ ነገር የለም።”

ጨዋታውን ማሸነፍ ያልቻሉበት ምክንያት …

“ያገኘነውን አለመጠቀም። ከአንድ ሁለት ዕድል አግኝተናል አልተጠቅምንም። የምታገኘውን ሳትጠቀም ስትቀር በእነኚህ አይነት አጋጣሚዎች ስህተቶች ልትሰራ ትችላለህ። ጫና እየበዛብህ ይመጣል ማለት ነው ፣ ያገኘህውን ሳትጠቀም ስትቀር ጫናው በተከላካይ ላይ ይሆናል እንደዚህ አይነት ስህተቶች ትሰራና ሊገባብህ ይችላል።”

ስለቡድኑ የአጨዋወት መንገድ…

“ያቃተን ማግባት ብቻ ነው። ያሉን ልጆች መጨረስ ካልቻሉ ጫናው እየጨመረ ይመጣል። ሰዓቱ በሄደ ቀጥር ልጆቹም ላይ ጫናው ይበዛል በእዛን ሰዓት ላይ መረበሽ ይመጣል። የሳቱትም ልጆች መረበሽ ይጀምራሉ ከኋላም ያሉት ሰዓቱ ሄደብን ብለው መረበሽ ይጀምራሉ። እንደዚህ አይነት ነገር ሲመጣ ስህተቶች ትሰራለህ አለመረጋጋት እንጂ በመጫወት ደረጃ ካለ ማስቆጠር በስተቀር የሚገባንን አድርገናል።”

ስለ ዳዋ ሆቴሳ ሚና…

“ዳዋ በብሔራዊ ቡድንም በሚጫወትበት ቦታ ነው ያጫወትነው። ባለፈው ከመቻል ጋር ሲሆን መሐል ላይ አስቀምጠነው ነበር። ስለሚመታ ሹት ስለሚያደርግ ኳሶች ረጃጅም ለአጥቂዎች ሲሰጥ ሁለተኛ ኳሶችን ለመጠቀም ነው። በዛሬው ቡድን ላይ ግን ራሱ በለመደው ቦታ ነው የተጫወተው እንደ ተጋጣሚም ነው የምትጫወተው ግን ዳዋ ባለፈው የአጥቂ አማካይ ነበር። ከዚህ በፊት አሸናፊ አሰልጣኝ የነበረ ጊዜ በብሔራዊ ቡድንም እዚህም የነበረ ጊዜ አጫውቶታል ቦታውን ያውቀዋል። ዛሬ ደግሞ የተጫወተው ደግሞ በብዛት የሚጫወትባቸው ቦታዎች ናቸው እና አዲስ ነገር አይደለም።”