ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጭማሪ ደቂቃ ግብ ጣፋጭ ድል ተጎናፅፏል

የግብ ዕድሎች በብዛት ባልተፈጠሩበት እና ለተመልካች ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀዲያ ሆሳዕናን በመጨረሻ ደቂቃ ግብ 1-0 ረቷል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ሲደረግ  ከመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች አንፃር በተደረጉ የአሰላለፍ ለውጦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሱለይማን ሀሚድ ፣ አዲስ ግደይ እና ኪቲካ ጀማን በገናናው ረጋሳ ፣ በረከት ግዛው  እና ሲሞን ፒተር ቦታ ሲጠቀም ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ሰመረ ሀፍተይን በማሳረፍ ለዳግም ንጉሴ እና ተመስገን ብርሀኑ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ሰጥቷል።

ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ባልተደረጉበት የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአጫጭር ቅብብሎች በመታገዝ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ በአንጻሩ ሀዲያዎች በረጃጅም ኳሶች እና በተለይም ዳዋ ሆቴሳን እና በየነ ባንጃን  የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።

ጨዋታው 21ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በነብሮቹ አማካኝነት ሙከራ ተደርጎበታል። ብሩክ እንዳለ በየነ ባንጃ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ሞክሮት በግቡ የላይ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሪችሞንድ ኦዶንጎ ከበየነ ባንጃ በተቀበለው ኳስ ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እየወሰዱ ቢሄዱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ንግድ ባንኮች 31ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ሙከራቸውን አድርገዋል። ዳግም ንጉሤ አዲስ ግደይ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ፉዓድ ፈረጃ ከረጅም ርቀት በቀጥታ ቢመታውም ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀሪ ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ በቀጠለባቸው የመጀመሪያ 35 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከሚታዩ የሚቆራረጡ ቅብብሎች እና ከሚደረጉ ጉሽሚያዎች እንዲሁም ዳኝነት ላይ ከሚነሱ ቅሬታዎች ውጪ በሁለቱም በኩል የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር።

የተሻለ እንቅስቃሴ በተደረገባቸው የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ውስጥ ግን ሀዲያ ሆሳዕና ቀይሮ ባስገባቸው ግርማ በቀለ እና ሠመረ ሀፍታይ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማጠናከር ችሎ ነበር። በዚህም 81ኛው ደቂቃ ላይ ሠመረ ሀፍተይ ከቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ  ያደረገው በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ  በረከት ወልደዮሐንስ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት ያደረጉት ሙከራም በዚሁ ለውጥ የተገኙ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

የጨዋታው ምርጡ የግብ ዕድል 87ኛው ደቂቃ ላይ በነብሮቹ ሲፈጠር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ንጹህ የማግባት ዕድል ያገኘው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መልሶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ከተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛው ደቂቃ ላይም በንግድ ባንክ በኩል ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሀዲያው ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ በግንባሩ ገጭቶ የራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል። በዚህም ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።