መረጃዎች | 11ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል ፤ ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

ወልቂጤ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የመጀመሪያ ድላቸውን የሚፈልጉ ቡድኖችን ያገናኛል።

በፈረሰኞቹ አራት ግቦች ተቆጥሮባቸው ሽንፈት በማስተናገድ ሊጉን የጀመሩት ወልቂጤዎች በተጠቀሰው ጨዋታ ትልቅ ዋጋ ያስከፈላቸው የግል ስህተቶች ፈፅመዋል። በነገው ጨዋታም በአሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት የድህረ ጨዋታ አስተያየት በመንተራስ በርካታ ለውጦች አድርገው እንደሚመለሱ መገመት ይቻላል። ወልቂጤዎች በአንዳንድ የጨዋታው አጋጣሚዎች ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በአጨዋወቱ የፈጠሯቸው ዕድሎች ጥቂቶች ነበሩ። በነገው ጨዋታም የግል ስህተቶቻቸው ከማረም ባልተናነሰ የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት ይዘው መግባት ግድ ይላቸዋል።

በመጀመርያው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የአንድ ለባዶ ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ሁለት መልክ ያለው የማጥቃት አጨዋወት አስመልክተውናል። በመጀመርያው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ በጨዋታው መገባደጃ ደግሞ በቀጥተኛ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ቡድኑ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ እና ባለፈው ጨዋታ በተከተለው አጨዋወት መሰረት የመልሶ ማጥቃት ቡድን ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ የመስመር አጨዋወት በሁለቱም ፈጣን ተጫዋቾች ቡልቻ ሹራና ይስሀቅ ካኖ መመራቱ ደሞ ሌላ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል፤ ለዚህ እንደሌላ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የረዣዥም ኳሶቹ መዳረሻ የነበረው ጋናዊው አጥቂ ፍሊፕ አጃህ መጎዳት ነው።

በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጉዳት የገጠመው ይገዙ ቦጋለ እና ጋናዊው አጥቂ ፊሊፕ አጃህ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ቡድናቸው አያገለግሉም። የወረቀት ሥራ የጨረሰው መሐመድ ሙንታሪ ግን በጨዋታው ሊሰለፍ ይችላል። በወልቂጤ በኩል የመሀል ተከላካዩ መሳይ ፓውሎስ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ለስድስት ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡናዎች አራቱን ጨዋታ በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርተው የዓምናውን የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 2-1 መርታት ችሏል።

ጨዋታውን ተፈሪ አለባቸው በመሐል ዳኝነት ፣ መሐመድ ሁሴን እና ዘመኑ ሲሳዬ በረዳት ዳኝነት ፣ ተስፋዬ ጉርሙ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ

በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ መረባቸውን ያላስደፈሩት ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ምሽት ላይ ይገናኛሉ።

አዲስ አዳጊውን ሻሸመኔ ከተማ አሸንፈው ሊጉን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ከዚህ ቀደም በአብዛኛው የሚታወቁበትን የረዣዥም ኳሶች አጨዋወት ለውጠው ነው ይህን የውድድር ዓመት የጀመሩት።

በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ስር ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን የገነቡት የጦና ንቦች ከሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በተጨማሪ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫም ተመሳሳይ አቀራረብ ነበራቸው። ቡድኑ ብዙአየሁ ሰይፈ፣ አብነት ደምሴ እና አበባየሁ ሀጂሶን ባካተተው የአማካይ ክፍል ጥምረት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርግም በተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚታየው የትኩረት ችግር ግን ከወዲሁ መላ ሊበጅለት ይገባል። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ በአጥቂ ክፍሉ የታየው የግብ ዕድሎች የመጠቀም ውስንነትም ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

ከባለፈው የውድድር ዓመት በብዙ መልክ የተቀየረ አጨዋወት ይዘው ከአዲስ አዳጊዎቹ ጋር አቻ የተለያዩት አዳማዎች በጨዋታው እምብዛም ጥንቃቄ የሚመርጥ አቀራረብ ይዘው ሊጉን ጀምረዋል። የአሰልጣኙ የባለፈው የውድድር ዓመት አቀራረብና እንዲሁም ያልተገመተው የዘንድሮው አጀማመር ስናይ የአዳማዎች የነገ ጨዋታ እቅድ ለመገመት አዳጋች ነው። ሆኖም የተጋጣምያቸው የወላይታ ድቻ የአማካይ ክፍል ጥንካሬ አዳማን እንደባለፈው ጨዋታ ጥንቃቄ የታከለበት አቀራረብ ይዞ እንዲገባ ሊያስገድደው ይችላል ተብሎ ይገመታል።

የአዳማ ከተማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም በወላይታ ድቻ በኩል ከተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

ሁለቱ ክለቦች ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ 16 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን በሦስት ጨዋታዎች ብቻ ነጥብ ሲጋሩ ወላይታ ድቻ ስምንት ጊዜ አዳማ ከተማ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

ለዚህ ጨዋታ ተካልኝ ደጀኔ በዋና ዳኝነት ፣ ሶርሳ ዱጉማ እና ደስታ ጉራቻ በረዳትነት እንዲሁም ዳንኤል ይታገሱ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።