ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

በምሽቱ ጨዋታ አዳማ ከተማ በኤልያስ ለገሰ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን 1-0 ረቷል።

የምሽቱ መርሐግብር ወላይታ ድቻን ከአዳማ ከተማ ሲያገናኝ ሁለቱም ቡድኖች ከባለፈው ጨዋታቸው አንፃር የአንድ ተጫዋች ቅያሪን አድርገዋል። ወላይታ ድቻ ጉዳት በገጠመው አናጋው ባደግ ምትክ አስናቀ አምታታው ሲተካ አዳማ ከተማ በበኩሉ በዮሴፍ ታረቀኝ ምትክ አሸናፊ ፊዳን አስገብቷል።

12፡00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት እና ከግብ ጠባቂ በመጀመር በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ወላይታ ድቻዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ሙሉ ብልጫውን መውሰድ ችለዋል።

መሃል ሜዳው ላይ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በነበረው አበባየሁ ሀጂሶ ጨዋታውን በማቀጣጠል እና ቢኒያም ፍቅሩን ዒላማ ያደረጉ የማጥቃት መንገዶችን በተደጋጋሚ ሲሞክሩ የነበሩት ድቻዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። ጸጋዬ ብርሃኑ ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አማካዩ አብነት ደምሴ በግንባሩ በመግጨት እና ከመሬት በማንጠር ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በቀኙ የግቡ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

አዳማ ከተማዎች ከራሳቸው የግብ ሳጥን ውስጥ ዝግ ያሉ ቅብብሎችን በሚያደርጉበት አጋጣሚ ስህተት በመሥራታቸው 18ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። በተሠራው ስህተት ኳስ ያገኘው ፍጹም ግርማ በግራው የሳጥኑ ክፍል ይዞት በመግባት ያቀበለውን ኳስ ቢንያም ፍቅሩ በደካማ አጨራረስ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም አጥቂው ከቀኝ መስመር ግብ ጠባቂውን ሰዒድ ሀብታሙን የፈተነ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው  መልሶበታል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ሲታትሩ የነበሩት አዳማዎች የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን 36ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መስዑድ መሐመድ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ዓይተን ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ አግዶበታል። በጥሩ ቦታ አያያዝ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በርካታ ኳሶችን ሳጥን ውስጥ ሲያገኝ የነበረው ቢኒያም ፍቅሩ 41ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሏል። ዘላለም አባተ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው በግሩም ሁኔታ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ፈታኝ የግብ ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ግን ማራኪ ፉክክር አድርገዋል።

በተመሳሳይ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ 76ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀይደር ሸረፋ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ኤልያስ ለገሰ ኳሱን በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ድቻዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ ሲቸገሩ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግም እስከ 81ኛው ደቂቃ ጠብቀዋል። ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥኑ ጫፍ ያደረገውን ይህን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መልሶበታል።

ብርቱ ፉክክር በተደረገባቸው የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ድቻዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ያላቸውን ኃይል ሁሉ ማጥቃት ላይ ሲያደርጉ 94ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሠርቶብናል በሚልም ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተው ነበር። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ብዙዓየሁ ሠይፈ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። ጨዋታውም ከዕረፍት መልስ ጠንካራ በነበረው አዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።