የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና

“እንደጠበቅነው ባይሆንም ዛሬ ተጫዋቾቼ ትልቅ እንቅስቃሴ ነው ያደረጉት” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት


“በብዙ ረገድ እኛ ራሳችንን ልናርም የሚገባን በርካታ ነገሮች አሉ” አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

በጭማሪ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በአቻ ውጤት ካጠናቀቁት ጨዋታ ፍፃሜ በመቀጠል አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ነበራቸው።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ብዙ በጠበኩት መልክ አልሄደልንም እንደ ዕቅዳችን ፣ ከዚህ ሙሉ ነጥብ ይዘን ለመሄድ ነበር ያሰብነው ፣ በብዙ ረገድ እኛ ራሳችንን ልናርም የሚገባን በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይ የተቃራኒ ቡድኖች ኳስ እንዲጫወቱ ነፃነትን መፍቀድ እኛም ያገኘነውን ኳስ በስርዓት ይዘን ወደ ትክክለኛው ቦታ አለማምራት የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አሁን ድክመቶች ይታይበታል። በዚህ ደረጃ ቀጣይ ጨዋታዎችን እያረምን መሄድ መቻል አለብን ይሄ ሁለተኛ ጨዋታ ነው ከጨዋታ ጨዋታ የሚያስምሩን ብዉ ነገሮች አሉ ያንን እያስተካከልን እንሄዳለን ብዬ አስባለሁ። እንደውሏችን ዛሬ ጥሩ ቀን አልነበረም።”

ከዕረፍት መልስ የኳስ ቀጥጥር ብልጫ ኖሯቸው በአጨራረስ ስለነበረባቸው ክፍተት…

“አሁንም ፊት ላይ አጃህም ህመም ላይ ነው ያለው ትልቅ አጥቂ የምለው ነው። አዲስ የመጣው ማይክልም ገና የመጀመሪያ ሊጉ ስለሆነ ብዙ የሚያሻሽላቸው ነጀሮች አሉ ፣ በተረፈ ከዕረፍት በኋላ የነበረው ከመጀመሪያው አጋማሽ ይሻላል ቢሆንም ግን ከዚህ በላይ መሄድ አለብን ብዬ እጠብቃለሁ።”

ቡልቻ ሹራን ለረጅም ደቂቃዎች ተጎድቶ ስለ መታገሳቸው…

“በመሠረቱ የህክምና ባለሙያው ይችላል ይቀጥል ስላለኝ ነው ፣ ያስቀጠልኩት ከእርሱም አንድ ነገር እንጠብቅ ነበር አልተሳካም ከእዛ በኋላ የቀየርኩት።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው …

“በጣም ደስ ይላል እንደጠበቅነው ባይሆንም ዛሬ ተጫዋቾቼ ትልቅ እንቅስቃሴ ነው ያደረጉት ከፀሀዩ ፣ ከአየሩ ሁኔታ አንፃር ዛሬ ጥሩ ነው አቻው ለሁለታችንም ጥሩ ነው ብዬ የማስበው።”

ከባለፈው ጨዋታ አንፃር በመከላከሉ ስለ ተወሰደው ዕርማት…

“በርግጠኝነት በተግባር ተጫዋቾቹ ላይም ያየነው እርሱ ስለሆነ ከዕለት ወደ ዕለት ይሄንን እየቀረፈ እንዲመጡ እኛም እናሰራለን ቀጣይ ጨዋታዎች ሁሉ ጠንካራ ስለሆኑ ትልቅ ሥራ ስለሚጠብቀን እያስተካከልን ስለምንገኝ ከዚህ በኋላም በዚሁ መንገድ ነው የምንቀጥለው።”

በተጋጣሚ በተቆጠረ ከደቂቃ በኋላ ግብ ማስቆጠር ስለሚፈጥረው ስሜት…

“ባለፈው ተሸንፈናል ፣ ዛሬ ደግሞ ከመሸነፍ ወደ አቻ የምንሆንበት ስለመጣን ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው ፣ ለምን አንድ ለባዶ እየተመራን ስለሆነ ፊሽካ መነፋቱ ስለማይቀር ለቡድናችን ለቀጣይ ጨዋታዎች ያነሳሳናል እና ለእኛ ነጥብ መያዛችን ትልቅ አድቫንቴጅ ነው።”

ስለ ራምኬል ሎክ እንዲሁም ስንታየሁ መንግስቱ ስለ ተቀየረበት ሒደት…

“የመጀመሪያ ጨዋታችን ላይ ስንታየሁን ነበር ከፊት ለፊት ያደረግነው ፣ ትንሽ አሞት ስለነበር ራምኬልን እዛ ጋር አድርገነዋል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ዝግጅት ላይ ሲሰራ ስለነበር ራምኬል እዚህ ጋር ነበር ሲፎካከር የነበረው እና ዛሬ ላይ ለዚህ ጨዋታ ይሆናሉ ብለን ስላሰብን እንደ አማራጭ ይዘነው ስለነበረ እስከ ስልሳ ሰባ ደቂቃ ድረስ ራምኬል ነበር ከዛ በኋላ ደግሞ ስንታየሁ ቀጠለን አስገብተናል ግን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል በሁለቱም ላይ ብዬ ነው የማስበው።”