የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-1 መቻል

“ብንረጋጋ ኖሮ ቢያንስ የተሻለ ውጤት ይዘን እንወጣ ነበር” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

“ተጫዋቾቻችን 90ውን ደቂቃ ሙሉ የሚችሉትን አድርገው ፣ በነበራቸው የሜዳ ላይ  ቁርጠኝነት አሸንፈን ልንወጣ ችለናል” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የጣናው ሞገድ ጦሩን ካሸነፈበት የ2ለ1 ውጤት መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለ ጨዋታው ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው ጥሩ ነው ፣ በእግር ኳስ መሸናነፍ ያለ ቢሆንም እንቅስቃሴው ጥሩ ነው ፤ ነገር ግን ብዙ የምናርማቸው ነገሮች አሉ።”

ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ስለ ማግኘታቸው …

“አይደለም ግቦቹ የገቡትን ዓይተህ ከሆነ በራሳችን ድክመት ነው ስለዚህ በእነዚህ ድክመቶቻችን ላይ እንሠራለን ፤ ሌላ የምለው ነገር የለም።”

ከዕረፍት መልስ ስለ ፈጠሩት ዕድል እና ስለባከኑ አጋጣሚዎች..

“አለመረጋጋት ነው ፤ ተጫዋቾቻችንን ብንነግራቸውም ጎልን ለማግባት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ መረጋጋት አልቻሉም ብንረጋጋ ኖሮ ቢያንስ የተሻለ ውጤት ይዘን እንወጣ ነበር።”

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ጠንካራ  ጨዋታ ነው። መቻል ከማሸነፍ ነው የመጣው ፣ የመቻል ስብስብ የሚከተሉት የጨዋታ ስብስብ እጅግ በጣም ጠንካራ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ያካተተ ቡድን ነው ፣ እኛ ደግሞ በመጀመሪያው ጨዋታ ነጥብ ጥለን ነው የዛሬን ጨዋታ ያደረግነው ፣ ለእኛ በጣም ፈታኝ ነበር ነገር ግን ተጫዋቾቻችን 90ውን ደቂቃ ሙሉ የሚችሉትን አድርገው በነበራቸው የሜዳ ላይ  ቁርጠኝነት አሸንፈን ልንወጣ ችለናል። ውጤቱም ይገባናል።”

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ አፈግፍገው ስለ መጫወታቸው…

“ከመሸነፍ ከመምጣታችን ጋር ተያይዞ ተጫዋቾች ላይ የሚፈጠር የስነ ልቦና ጫና ይኖራል ፣ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረን እየመራን የነበረበት ሁኔታ ነው ፣ ግን በእነዛ መካከል የምንፈጥራቸውን የግብ ዕድሎች ያለመጠቀም ክፍተቶች ይታያሉ። እንዳልከውም ደግሞ አንድ ጎል ካስተናገድን በኋላ 2ለ1 ሆነን በተከታታይ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለት ሦስት ኳሶችን ያገኘንበት ሁኔታ ነበር። እነዛ ደግሞ የጨዋታውን መልክ የበለጠ ተጫዋቾቼን ተረጋግተን እንዲጫወቱ የበለጠ የማድረግ ዕድል ነበራቸው ግን አልሆነም ፤ ሀብታሙ የሚችለውን ጥረት አድርጓል ይህንን ደግሞ የማረም የማስተካከል ስራ በቀጣይ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።”

ዛሬ በግራ ተከላካይነት ስለ ተሰለፈው ፍፁም ፍትህአለው እንቅስቃሴ…

“ፍፁም ከታች ከቢ ቡድን የተገኘ ተጫዋች ነው። በተፈጥሮ የመሐል ተከላካይ ተጫዋች ነው ፣ ነገር ግን ፍራኦል እዚህ ቦታ ላይ በመጎዳቱ በሌላ ተጫዋች ባለፈው ሳምንት ለመጫወትም ሞክረናል ፣ ዋጋ ከፍለን የወጣንበት እንቅሰቃሴ ነበር የነበረው ፣ ዛሬ ለዚህ ለወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥተን ነው ያስገባነው። እንደ መጀመሪያ የሜዳ ላይ ቆይታው ፣ ከቦታ አያያዙም አኳያ እጅግ ደስ የሚል እንቅስቃሴ ነው ያደረገው ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ ያለው ተጫዋች ነው።”