የአሰልጣኞች አሰተያየት | ሻሸመኔ ከተማ 0-1 ሀዋሳ ከተማ

“በግብ ጠባቂያችን መዘናጋት ውጤቱን ልናጣ ችለናል ፣ ይሄ ውጤት አይገባንም ነበር” አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ

“እንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ለቡድናችን በጣም አስፈላጊ ነው” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

የሳምንቱ ማሳረጊያ በሆነው እና ሀዋሳ ከተማ በእዮብ ዓለማየሁ ብቸኛ ግብ ሻሸመኔ ከተማን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ በተከታዩ መልክ ሰጥተዋል።


አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ – ሻሸመኔ ከተማ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታውን እንግዲህ ለማሸነፍ ነበር የመጣነው። በደንብ ካለፈው ስህተታችን አርመን ዛሬ ሙሉ ለሙሉ እንደታየው ሜዳ ላይ የተሻለ ቡድን ይዘን ነበር የቀረብነው ፤ ድንገት በግብ ጠባቂያችን መዘናጋት ውጤቱን ልናጣ ችለናል ፣ ይሄ ውጤት አይገባንም ነበር።”

ከመጀመሪያው አጋማሽ ፣ በሁለተኛው ስለ መቀዛቀዛቸው…

“ባለፈው ጨዋታ ውጤት ስለጣልን ፣ በተቻለ አቅም ነጥብ ይዘን ለመውጣት ነበር ሀሳባችን ፣ ያንን የጥንቃቄ ጨዋታ እንዲያደርጉ ነበር ለተጫዋቾቼ የነበርኳቸው ፣ በመከላከል ውስጥ ሆነው የማጥቃት ሥራችንን እንድንሠራ ነበር ፣ የእዛን ያህል በዘጠና ደቂቃ ውስጥ በሀዋሳ በኩል የተሞከረ ሙከራ ብዙም የለም ግን አጋጣሚ ሆኖ ፣ መቀዛቀዝ ያልከው የጨዋታ ስትራቴጂ ነው ለምን በመከላከል ውስጥ ሆነን የማጥቃት ሥራችንን ተረጋግተን ያቺን ደቂቃ ለማሳለፍ ነበር የሞከርነው ግን የሆነው ሆኖ ተሸናፊ ሆነናል አይገባንም ነበር ውጤቱ።”

በተጫዋቾች ላይ ስላለው ፍላጎት እና ስለሚታየው የልምድ ማነስ…

“ከመጀመሪያው ጨዋታ ዛሬ በጣም የተሻለ ነው። ቡድናችን በጣም ፕሮሚሲንግ የሆነ እንቅስቃሴ ነው ያደረገው ዛሬ ደግሞ ያየነውን ችግር እንሠራበት እና አስተካክለን እንቀርባለን ስለዚህ ዕርግጠኛ ነኝ የተሻለ ቡድን ውጤታማ የሆነም ቡድን ይዘን እንቀርባለንም ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በኋላ የሚገጥሙንም ጠንካራ ናቸው ብዬ አስባለሁ ለእነርሱም ግድ ዝግጅት ያስፈልገናል ፣ ማንም ይሁን ሊጉ ላይ ተፎካካሪ ሆነን እንደምንቀርብ ዕርግጠኛ ነኝ።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው እንዳሰብነው ነው። እንደሚጠነክር ምንም ጥያቄ የለውም ፣ አንደኛ ሻሸመኔ ከሸንፈት ነው የተመለሰው ፣ እኛ ከአቻ ነጥብ ነው የመጣው ጠንካራ ጨዋታዎችን አድርገን ነው የመጣነው ምክንያቱም ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ ለእኛ ከምንም በላይ ነው። ስቴፑን ጠብቆ ለመሄድ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎችን ማሸነፍ በጣም ለቡድናችን አስፈላጊ ነው። በተለይ ጎሎች አለማግባታችን ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ወደ ጭንቀት ውስጥ ተጫዋቾቻችን እየገቡ ነበር የተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ  ፣ እንቅስቃሴውንም የአቋቋም ለውጥም በማድረግ የምንፈልገውን ሦስት ነጥብ አሳክተናል ብዬ አስባለሁ።”

የተጫዋቾችን የሚና ለውጥ በተደጋጋሚ ስለ ማድረጋቸው…

“ከልምምድ ባሻገር መጀመሪያ ተጫዋቾቹንም ስሰበስብ ቡድኑ ውስጥ ብዙ ኳሊቲ ያላቸው ፣ ብዙ ቦታ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው። ስለዚህ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ማሸነፍ ነው ከምንም በላይ ከአንተ የሚጠበቀው እና በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ በምትፈልገው መንገድ መጓዝ ካልቻለ ቡድኑ የተጫዋቾች ቅያሪ እናደርጋለን ፣ የቦታ ለውጥ እናደርጋለን ፣ የፎርሜሽን ለውጥ እናደርጋለን ስለዚህ ባለፈውም በዚህ መንገድ ነው ነጥብ የወሰድነው ዛሬም ደግሞ ያሸነፍነው ፣ ከተጫዋቾቹም ኳሊቲ አንፃር ነው እኛም ስንሰራበት ስለነበር ተጫዋቾች ሲገቡ አዲስ አይሆንባቸውም የሠራንበት መንገድ ነው።”

ስለ እዮብ ዓለማየሁ ድንቅ ግብ…

“እዮብ የሚያሳየውን እንቅስቃሴ የሚገልጸው ምክንያቱም እዮብ ባለፈውም ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ነው ያመሸው ዛሬም ያስቆጠረው ጎል የእርሱን እንቅስቃሴ የሚገልጽ ጎል ነው ብዬ ነው የማምነው።”