ሪፖርት | ሀምበሪቾ እና ሀዲያ ነጥብ ተጋርተዋል

ቀዝቃዛ ፉክክር የተደረገበት የሀምበሪቾ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ከድል የራቁት ሀምበሪቾ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በሦስተኛው ሳምንት አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪን አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል። ሀምበሪቾዎች ትዕግስቱ አበራን በዲንክ ኬር ፣ የኋላሸት ፍቃዱን በአቤል ከበደ ሲለውጡ በሀድያዎች በኩል ደግሞ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎ አርፈው በዘካሪያስ ፍቅሬ እና ተመስገን ብርሀኑ ተተክተዋል።


መጠነኛ ፉክክር በታየባቸው የመጀመሪያ 2ዐ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ፈጥነው ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ግን 19ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾው አፍቅሮት ሰለሞን ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ አድርጎ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ሁለቱም ቡድኖች በተለይም ሀዲያዎች ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመከተል ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ ሲገቱ በአንጻሩ ሀምበሪቾዎች መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ አልፎ አልፎ የሚታይ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በአጋማሹ የመጨረሻ 5 ደቂቃዎች ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ቢቀጥልም በሁለቱም በኩል ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚታየው ደካማ እንቅስቃሴ ጨዋታውን አሰልቺ አድርጎታል። ሆኖም ግን 44ኛው ደቂቃ ላይ ነብሮቹ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን የተሻለ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በደንብ ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ብርሃኑ በደካማ ውሳኔ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በመግባት ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 49ኛው ደቂቃ ላይ የኳስ ቁጥጥር መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዲያዎች ተጨማሪ ዱብ እዳ ገጥሟቸዋል። በረከት ወልደዮሐንስ ከሀምበሪቾው ዳግም በቀለ ጋር በገባው ሰጣ ገባ የቢጫ ካርድ ቢመለከትም በሴኮንዶች ልዩነት በድጋሚ ለፀብ በመጋበዙ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።


በሁለቱም በኩል በሚደረጉ የተቆራረጡ ቅብብሎች ጨዋታው እጅግ እየተቀዛቀዘ ሄዶ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ቀጥሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ መጠነኛ መሻሻል ያሳዩት ነብሮቹ በአንጻራዊነት የሀምበሪቾን የግብ ክልል ለመፈተን ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራውን የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ለመግባት እጅግ ተቸግረዋል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በተቸገሩት ሀምበሪቾዎች በኩልም ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢደረግም 88ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር አድማሱ ከሳጥን አጠገብ ካደረገው ሙከራ ውጪ ባልተረጋጋ ሂደት ሲባክን ተስተውሏል። ሆኖም ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።