የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀምበርቾ 0-0 ሀዲያ ሆሳዕና

“ለቡድኑ ምንም የማይጠቅም ስራ የሚሰሩ ተጫዋቾችን እኔ አልደግፍም” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

“እግር ኳስ ነው በቁጥር ብትበልጥም ሊገባብህ ልትሸነፍ የምትችልበት መንገድ አለ” አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ

0-0 ከተቋጨው የተራራ አናብስቶቹ እና የነብሮቹ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለ ጨዋታው ቆይታ አድረገዋል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው እና ስለ በረከት ወልደዮሐንስ ቀይ ካርድ…

“ማድረግ የሚገባንን በአንደኛው አጋማሽ ማድረግ ነበረብን ፣ ብዙ አጋጣሚዎች አገኘን ግን አሁንም ክለባችን ችግሩ መጨረስ ነው። የመከላከል ችግር የለብንም ጎል አንሰጥም አደገኛ ነገሮች እንዲፈጠሩ አናደርግም ፣ የዛሬም እንዳየህው በረኛችን ኳስ ሳይዝ ነው የወጣው ሦስት መደዳውን ጨዋታዎች አንድም ኳስ አልነካም። በረኛ ዘጠና ደቂቃ ተከላክሎልህ መጫወት አይችልም ፣ ሞራል ልሰጠው የምትችለው ለተከላካይ እና ለበረኛ ስታገባለት ነው ፣ አሁን በማግባቱ ላይ ችግር አለብን ያንን በደንብ መስራት ይኖርብናል። ተከላክለህ በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ መውጣቱ በየጨዋታው ሁለት ነጥብ እየጣልክ ስለምትመጣ ጥሩ አይደለም ግን ለዛሬው በአስር ተጫውተን ከዕረፍት በኋላ ያገኘነው ውጤት ጥሩ ነው። ነገሮች መቀየር ከነበሩባቸው በመጀመሪያ ላይ ነበር ፣ እንደዚህ አይነት ነገር ሲመጣብህ እና ዲሲፕሊን አጥቶ ለቡድኑ ምንም የማይጠቅም ስራ የሚሰሩ ተጫዋቾችን እኔ አልደግፍም። አንደኛ ጓደኞቹ ላይ ከፍተኛ ጫና ነው የሚፈጥረው ፣ ሁለተኛ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ጫና ነው የሚፈጥረው ፣ ሦስተኛ ነባር እና ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። እንደነኚህ አይነት ነገሮችን ከኳስ ጋር ባልተገናኘ ምንም በማይጠቅም ነገር በቀይ መውጣት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም መቶ በመቶ እንቃወማለን መደረግም አይገባውም ያ ደግሞ ጫናም ባይኖርብን የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ግን ሰው ሲጎልብህ የአንድ ተጫዋች ስራ ተጨማሪ እያደረክ ነው የምትሰራው ፣ አስር ለአስራ አንድ ሲሆን መከላከል ላይ አጥቂው ወደ መሐል ይመጣል ያኔ የሚያጠቃ ሰው የለም መሐል ሜዳ ያለው ወደ ፊት አይሄድም ፣ ተከላካዩን ሲረዳ ይወርዳል ግን በጥሩ ጫና ባልፈጠሩበት ሁኔታ መጨረስ ችለናል።

የአማካይ ተጫዋቾች የማጥቃት ተሳትፎ መዳከም…

“እኛ የተነጋገርነው ሦስት የመሐል ሜዳ ተጫዋቾቻችን ወደ ኳስ መጥታችሁ ተቀበሉ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጉጉት ይኖራል ፣ እንገባለን እናሸንፋለን የሚል ይቅር እና የተሰጠህን አሳይመንት ትረሳለህ እኛ እንደውም ያልነው ወደ ኳስ እየመጣን ኳሱን በመቀበል ተጫወቱ ነው ፣ ብዙ ጊዜ የእኛ የመሐል ተከላካዮች ኳስ ይዘው ይቆሙ ነበር የሚቀበላቸው እያጡ ስለዚህ የተነጋገርነው ሌላ ነው ተጫዋቾቹ ያደረጉት ሌላ ነው ፣ ማፈግፈግ የሚባለው ነገር በፍጹም እንኳን በ10 ሰው በ11ም ሰው አፈግፍጉ አላልንም ፣ እንደውም በ10 ሰው ሁለት አጥቂ አድርገን ነበር የተጫወትነው በፊት በአንድ ነበር የምንጫወተው መከላከል ከፊት ስለነበር የሚጀመረው እዛው እንጫናቸው ነበር።”

በማጥቃቱ ከፍ ያለውን ቡድን መቼ እንጠብቅ…

“ማሰራት ትችላለህ ፣ ጎል ማግባት ተፈጥሯዊ ነው። ያቺ ብረት ውስጥ ኳስ መክተቱ ተጫዋቹ ዲሲፕሊን ያለው ፣ ተጫዋቹ የተረጋጋ ፣ ተጫዋቹ ነገሮችን በጣም ማንበብ የሚችል መያዝ አለብኝ ወይ መልቀቅ አለብኝ ወይ ከሌላ ጋር መጫወት አለብኝ ወይ ሹት ማድረግ አለብኝ የሚለውን መዓት ጥያቄ የሚገባቸውን ማሟላት ይገባል። እንደርሳለን የመድረስ ችግር እኮ የለብንም መጨረስ ላይ አዎ ወጣት አጥቂዎች አሉን ፣ ምክንያት ግን መሆን አይገባውም። ቡናን እንመልከት በጣም ብዙ ወጣቶች ያሉበት ቡድን ነው ግን ስራቸውን እየሰሩ ነው። በምንችለው መጠን በየልምምዱ እየሰራንም ያለነው በትልልቁ በኢንተርናሽናል ደረጃም ስንመለከት እኮ አንዳንድ ጊዜ ስድስት ወርም ስምንት ወርም ጎል የማያገቡ አጥቂዎች አሉ ፣ የእኛ ያ አይደለም የእኛ ደግሞ መስራቱ ነው ችግር የሆነብን ፣ እነኛ ላያገኙ ይችላሉ ኳስ ላይደርሳቸው ይችላል። ያንን በስራ እናመጣለን የሚል እምነት አለኝ።”

አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ – ሀምበሪቾ

ስለ ጨዋታው …

“ዛሬም ሦስት ነጥብ ለማግኘት ጥረት አድርገናል ፣ ጉጉትም አለ መጥፎ አይደለም ብዙ ኳሶችን ሄደናል። ትንሽ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ያለመረጋጋቶች ነበሩ መጥፎ አይደለም።”


ከኳስ ቁጥጥር ብልጫቸው አንፃር የጠሩ የጎል ዕድሎች አለመፍጠራቸው…

“እውነት ነው። ዛሬ እንደውም ከሌላ ጊዜ ነፃ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ፣ በተከላካይ ላይ የነበረብን ቦታ ጥሩ ሆኖ ሳለ ዛሬ ደግሞ ያንን ለማሳካት ነበር ወደ ሜዳ የገባነው ፣ ምንአልባት ይሄ ሦስት ነጥብ አለማግኘት ተጫዋቾቹ ላይ ጉጉት አሳድሯል እላለሁ። ከዛ አንግል ትክክል ነው ሌላ ቀን የፈጠርናቸውን የጨዋታ ብልጫ አለን ግን ንፁህ የጎል ዕድል ላይ እንደሌላ ቀን ዛሬ አይደለንም። ከጉጉት የተነሳ ነው ይሄንን አስተካክለን እንመጣለን።”

ሀድያ ሆሳዕናዎች ከ50 ደቂቃዎች በኋላ በቀይ ካርድ ተጫዋች በማጣታቸው የቁጥር ብልጫን መጠቀም አለመቻላቸው…

“ማድረግ ያለብንን ሁሉ አጥቂዎችን ነው የተጠቀምነው ፣ ለማጥቃት ከፈለግነው ሁኔታ ሁሉንም ሄደናል። እነርሱ ሳጥን አካባቢ ነው ያለነው አንዳንዴ በረጅሙ ሰዓት በማባከናቸው እንዳሰብነው እንዳይሆን አድርጎታል። አጥቅቶ ለመጫወት ሁሉንም ነገር አድርገናል። እግር ኳስ ነው በቁጥር ብትበልጥም ሊገባብህ ልትሸነፍ የምችልበት መንገድ አለ።”

የእስከአሁኑ የቡድኑ ጥንካሬ..

“ጠንካራ ነው የምለው ኳስ ተቆጣጥሮ እንደ ቡድን የምንጫወተው ጥሩ ነው። ከዚህ ቀደም ያልነበረው ዛሬ ተስተካክለ የምለው የመከላከል ዲፓርትመንቱ የተሻለ ነገር አይተናል። ቀጣይ በዕርግጠኛነት ወደ ሦስት ነጥብ ለመሄድ እንዘጋጃለን።”