ሪፖርት | ፈረሠኞቹ በሁለት ግብ ከመመራት ተነስተው ነጥብ ተጋርተዋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ እጅግ ማራኪ ፉክክር ተደርጎበት 2-2 ተጠናቋል።

በምሽቱ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ሲገናኙ ፈረሠኞቹ ከሻሸመኔው ድል የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ፋሲል ገብረሚካኤልን በባህሩ ነጋሽ እና  ረመዳን የሱፍን በሻሂዱ ሙስጠፋ ሲለውጡ ከሀምበሪቾው የአቻ ውጤት አንፃር አዳማዎች የአራት ተጫዋቾችን ቅያሪ ማድረግን መርጠዋል። መላኩ ኤልያስ ፣ ሱራፌል ዐወል ፣ አድናን ረሻድ እና ቢኒያም አይተን ወጥተው ሐቢብ መሐመድ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ መስዑድ መሐመድ እና ዮሴፍ ታረቀኝ በቋሚነት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ማራኪ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የታዩበት ነበር። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 12ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዊልያም ሰለሞን ከግራ መስመር ወደ ግብ ሲመታ ሄኖክ አዱኛ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት የፈረሠኞቹ የቀድሞ ተጫዋች ሀይደር ሸረፋ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ፈረሠኞች 14ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው ነበር። ሆኖም ግን ተገኑ ተሾመ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ የተሳካ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፈው የመሃል ተከላካዩ ፍቅሩ ዓለማየሁ ተደርቦ አስወጥቶበታል።

መምራት ከጀመሩ በኋላ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት አዳማዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ አንጋፋውን አማካይ መስዑድ መሐመድ በጉዳት ምክንያት በቻርለስ ሪባኑ ለመቀየር ቢገደዱም በፈጣን ሽግግሮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን ግን ሲቀጥሉ ተስተውሏል። ሆኖም ግን ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅሰቃሴ የፈጠሯቸውን የግብ ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።

በአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እየወሰዱ የሄዱት  ፈረሠኞች 43ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከፍ አድርጎ ባቀበለው እና አቤል ያለው ኳሱን ሳይደርስበት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በያዘበት ኳስ የአዳማን የተከላካይ መስመር መፈተን ሲችሉ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ሻሂዱ ሙስጠፋ ከግራ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ግብ ቢሄድም ሰዒድ ሀብታሙ ጨርፎ ወደ ውጪ አስወጥቶታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሜዳው ዕረፍት ላይ በጣለው ዝናብ ኳስ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ቢሆንም በሁለቱም በኩል ያለ ማቋረጥ የሚደረገው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታው ለተመልካች ሳቢ ፉክክር ተደርጎበታል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የጨዋታ ስሜት ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት አዳማዎች ተሳክቶላቸዋል 53ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ዮሴፍ ታረቀኝ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ በጥሩ ክህሎት ገፍቶ በወሰደው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ሲመልሰው ኳሱን ያገኘው ዊልያም ሰለሞን አስቆጥሮታል።

በሁለት ግብ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ጊዮርጊሶች 65ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ሞሰስ አዶ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ ጥፋት የተሠራበት በሚመስል ሰዓት የአዳማ ተከላካዮች ሲዘናጉ በመሃላቸው ገብቶ ኳሱን ያገኘው አቤል ያለው ተደርቦ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ተገኑ ተሾመ ግብ አድርጎታል።

ከነበራቸው የጋለ የማጥቃት እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዙ የሄዱት አዳማዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ እና ኳሱን በመቆጣጠር ውጤቱን ይዘው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም የፈረሠኞቹን ጫና ለመቋቋም ሲቸገሩ ተስተውሏል። እጅግ ማራኪ የጨዋታ ፍሰት እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ የፈረሠኞቹ የመስመር አጥቂ ተገኑ ተሾመ 82ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መልሶበታል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በመጨረሻ ደቂቃዎች ሞሰስ ኦዶን ፣ በረከት ወልዴ እና አሮን አንተርን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን እጅግ ሲያጠክሩ የአሰልጣኙ ቅያሪም ውጤታማ ለመሆን ብዙ አልፈጀበትም። 83ኛው ደቂቃ ላይ አሮን አንተር ሰንጥቆ ባቀበለው ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ሮጦ የገባው ሞሰስ አዶ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ወደ ነበሩበት ግለት የተመለሱት አዳማዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት በወጣበት ኳስ የፈረሠኞቹን ሳጥን ፈትነው ሲመለሱ የጨዋታው መጠናቀቂያ 95ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤልያስ በግሩም ክህሎት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ወደ ሳጥን ቢገባም ሙከራው በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።