መረጃዎች| 30ኛ የጨዋታ ቀን

በነገው ዕለት የሚደረጉ የስምንተኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ !

ፋሲል ከነማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

ፋሲል ከነማና ሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርጉት የነገው የመጀመርያው መርሀ ግብር ይሆናል።

ባለፈው ሳምንት ከተከታታይ የአቻና የድል ውጤቶች በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱት ዐፄዎቹ ከሽንፈት ለማገገም ሀድያን ይገጥማሉ። ዐፄዎቹ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በሁሉም ረገድ በጥሩ የመሻሻል ሂደት ውስጥ ነበሩ፤ በጦና ንቦች በተሸነፉበት ጨዋታ ግን ከወትሮው በተለየ ደካማ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
ከኳስ ውጪ በጋለ እንቅስቃሴ ጫና ለመፍጠር የሞከሩትን የወላይታ ድቻ አማካዮች ጫና ተቋቁመው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲቸገሩ የተስተዋሉት ዐፄዎቹ በጨዋታው የጠራ የግብ ዕድሎች አልፈጠሩም።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ የግብ ዕድል መፍጠርያ አማራጮች ማስፋት ይጠበቅባቸዋል። የነገው ተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ መንገድ በቁጥር በዝቶ ለመከላከል የሚሞክር ቡድን እንደመሆኑ ተመሳሳይ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎም ይገመታል። የዐፄዎቹ የተከላካይ መስመር ምንም እንኳ ከአራት ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ተፈትኖ ሁለት ግቦች ቢያስተናግድም በነገው ዕለት ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ አይገመትም። ሆኖም ሀድያዎች ያላቸው የፈጣን ተጫዋቾች አቅም መጠቀም ከቻሉ አደጋ የማይፈጥሩበት ዕድል የለም ማለት አይቻልም። ለምን ቢባል የዐፄዎቹ የተከላካይ ክፍል ፈጣን አጥቂዎች ካሉት ቡድን ጋር ሲገናኝ እንደሚቸገር ከሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጋር ያደረጓቸው ጨዋታዎች መለስ ብሎ መመልከት ይቻላል።

አምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በአምስት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሀድያዎች በጨዋታ በአማካይ 0.4 ግቦች ብቻ ያስመዘገበ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው። ቡድኑ ኢትዮጵያ መድንን በገጠመበት ጨዋታ ላይ ከአራት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ግብ ማስቆጠር ቢችልም የመረጠው የረዣዥም ኳሶችና ፈጣን ሽግግር የማጥቃት አጨዋወት ስኬታማነት ግን እንደሚፈለገው ስል አልነበረም። በነገው ጨዋታም በተጠቀሰው መንገድ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ይቸገራሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ውስን የአጨዋወት መንገድ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ለሳምንታት የቆየው የመከላከል ጥንካሬው ማስቀጠሉ አንድ በጎ ጎን ነው። በነገው ጨዋታም ከዐፄዎቹ አጥቂዎች የሚያደርጉት ፍልምያ የጨዋታው ወሳኝ ነጥብ ይሆናል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ከኬኒያው የሴካፋ የትምህርት ቤቶች ውድድር መልስ በመሐል ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ወጋየሁ አየለ በረዳትነት አዲሱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።

ፋሱል እና ሀዲያ ሄሳዕና ከዚህ ቀደም ለስድስት ጊዜያት ሲገናኙ ፋሲል ከነማ ሁለቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይወስዳል። ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ዐጼዎቹ ስድስት ነብሮቹ ደግሞ ሦስት ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

በመጨረሻው ሳምንት ሁለት ሁለት ግቦች አስቆጥረው ማሸነፍ የቻሉት ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ ምሽት ላይ ይከናወናል።

ሲዳማ ቡናን ሁለት ለባዶ አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ ስምንት ከፍ ማድረግ የቻሉት ብርቱካናማዎቹ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ያገኙትን ድል ለማስቀጠል የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ። ድሬዎች በመጀመርያዎቹ ሳምንታት የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚቸገር የአማካይ ጥምረትና ያልተደራጀ የማጥቃት ክፍል ነበራቸው። ከአራተኛው ሳምንት በኋላ ግን መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል፤ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በአማካይ 1.5 ግቦች ማስቆጠራቸውም የመሻሻላቸው አንድ ማሳያ ነው።

በሊጉ ጅማሮ ጠንካራ የነበረውና በአራተኛው ሳምንት ጨዋታ በባንክ ተፈትኖ ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉም ከድክመቱ አገግሞ ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለሱም ከቡድኑ ውስጥ ከታዩት በጎ ጎኖች አንዱ ነው፤ በነገው ጨዋታም ከሊጉ አስፈሪ የማጥቃት ጥምረት አንዱ ከሆነው ከጣና ሞገዶቹ የአጥቂ ክፍል ቀላል የሚባል ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ አይታመንም፤ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ለፈጣን ሽግግሮች በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ መግባትም ይጠበቅበታል።

ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው ነጥባቸው አስራ አራት ያደረሱት ባህርዳር ከተማዎች የሊጉ መሪዎችን እግር በእግር መከታተላቸውን ቀጥለዋል። የጣና ሞገዶቹ በሰባት ጨዋታዎች አስራ ሦስት ግቦች ያፈራ የማጥቃት አጨዋወታቸው የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ነው። በፈጣን ሽግግሮች ላይ የተመሰረተ ማጥቅያ መንገድ ያላቸው የጣና ሞገዶቹ ከፋሲሉ ጨዋታ ውጭ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡበት ጨዋታ የለም።

በጨዋታ በአማካይ 1.8 ግቦች ማስቆጠራቸውንም የቡድኑ አጥቂ ክፍል ስልነት ያመላክታል፤ ቸርነት ጉግሳ ከጥሩ እንቅስቃሴ አልፎ በግቦች ተሳታፊ መሆን መጀመሩም የአጥቂ ጥምረቱን ይበልጥ አጠናክሮታል። ቡድኑ ከተጠቀሰው አጨዋወት ውጭ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረትም ይስተዋላል፤ በተለይም ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ከሳጥን ውጭ በሚመቱ ኳሶች ተበራክተው ነበር። በነገው ጨዋታም ተጋጣምያቸው ጥቅጥቅ ብሎ የሚከላከልበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ መሰል ሙከራዎች መኖራቸው አይቀሪ ነው።

ድሬዳዋ ከተማዎች አሁንም የያሲን ጀማል፣ አብዩ ካሳዬና ኤፍሬም አሻሞ ግልጋሎት አያገኙም፤ ከዚህ በተጨማሪ ከጉዳት መልስ ቡድኑ በጥሩ መንገድ ማገልገል ጀምሮ የነበረው ተመስገን ደረስ በጉዳት ምክንያት ቡድኑን አያገለግልም። የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው የአደም አባስ ግልጋሎት አያገኙም።

ኢንተርናሽኛል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በተከታታይ ከመራቸው የአፍሪካ የክለቦች የማጣሪያ ጨዋታዎች ተመልሶ በዋና ዳኝነት ሲዳኘው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት ሲመሩ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።

የስምንት ጨዋታዎች ግንኙነት ያላቸው ቡድኖቹ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በድምሩ አስራ ስድስት ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን አራት ድሎችን ያስመዘገቡት ባህር ዳሮች አስር እንዲሁም አንድ ጊዜ ያሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ስድስት ግቦችን አስመዝግበዋል።