መረጃዎች| 31ኛ የጨዋታ ቀን

ስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ይደረጋሉ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ንግድ ባንኮች በድጋሜ መሪነቱን ለመቆናጠጥ ቡናማዎቹ ደግሞ ከአራት ተከታታይ ድል አልባ ጉዞ ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ተከታታይ አራት ጨዋታዎች አሸንፈው ነጥባቸውን አስራ ሰባት ማድረስ የቻሉት ንግድ ባንኮች ወደ ሊጉ መሪነት ለመመለስ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። ባንክ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቅ መሻሻል ያሳየ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው፤ የማጥቃት ጥምረቱ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አስር ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ብቃት ላይ ይገኛል። በሊጉ አራት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍልም ቢሆን በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ ጥምረት ነው። ንግድ ባንኮች በመጀመርያው አጋማሽ አጥቅተው በመጫወት ጨዋታውን በመጀመርያው 45′ ለመጨረስ የሚሞክር ቡድን ነው፤ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው አስር ግቦች ስምንቱ በመጀመርያው አጋማሽ የተመዘገቡ መሆናቸውና የአጋማሹ የቡድኑ እንቅስቃሴ ለዚ ማሳያ ነው።
በነገው ጨዋታ ግን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በመጀመርያ አጋማሽ ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ቡድን እንደ መግጠማቸው እንደከዚ ቀደም በመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታውን ጨርሰው የሚወጡበት ዕድል ሰፊ ነው ተብሎ አይገመትም። ቡናዎች ከተቆጠሩባቸው ስምንት ግቦች ስድስቱ በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ የተቆጠሩ ናቸው። ሆኖም ጨዋታው ለንግድ ባንክ ወሳኝ እንደመሆኑ እንደወትሮው ኳስ ተቆጣጥረውና አጥቅተው ይጫወታሉ ተብሎ ይታመናል።

የመጀመርያ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው ሊጉን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዛ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። በሁለት ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ በተቀሩት ሁለት ደግሞ ሽንፈት አስተናግደዋል። ቡናማዎቹ በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ምንም ግብ ያላስተናገደ ጠጣር የተከላካይ ክፍል ነበራቸው። ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ ግን የመከላከል ጥንካርያቸው አጥተው በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች በማስተናገድ ደካማ ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል፤ በነገው ጨዋታ ግን በሊጉ አስራ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት ጥምረት ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ይህንን የቡድኑ ድክመት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡናማዎች ከሌላው የቡድኑ ክፍሎች በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት ክፍል አላቸው፤ የማጥቃት ክፍሉ ምንም እንኳ በየጨዋታው በአማካይ 1.25 ግቦች ብያስቆጥርም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ተስፋ ሰጪ ነው። በነገው ጨዋታም መሰረታዊ ለውጥ ከሚያስፈልገው ደካማ የመከላከል ጥምረት ከማስተካከል ባለፈ የማጥቃት ክፍሉ ጥራትም ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እስካሁን የተረጋጋ የአጥቂ ጥምረት የሌላቸው ሰርብያዊው አሰልጣኝ በነገው ዕለት የሚጠቀሙበት ጥምረት ለመገመት ያዳግታል።

ንግድ ባንኮች በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በቡና በኩል ግን ሬድዋን ናስር፣ አብዱልከሪም ወርቁና ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።

ከ2009 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 34 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 18 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። ባንክ 8 ሲያሸንፍ በቀሪው 8 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 53 ጎሎች ፣ ባንክ 35 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።


ሀምበሪቾ ከ ኢትዮጵያ መድን

በአራት ነጥብ የሚበላለጡ ክለቦች ስለሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ሀምበሪቾዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ወይም ከሳምንታት በኋላ ነጥብ ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀምበሪቾዎች የማጥቃት አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል፤ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎችም ኳስና መረብ አላገናኙም፤ ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ማሸነፍ እንኳ ባይችልም መጥፎ የሚባል የማጥቃት ክፍል አልነበረውም፤ በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦችም ማስቆጠርም ችሎ ነበር። አሁን ግን ይሄንን ጥንካሬውን አጥቷል፤ አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞም ይህንን የቀደመ የቡድኑ ጥንካሬ ማስመለስ ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይጠበቅበታል። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች በመስመሮችና በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም ውጤታማነቱ ግን ዝቅተኛ ነበር። ሀምበሪቾዎች በወሳኙ የጨዋታ ክፍል ማለትም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግቦች አስተናግደው ለመሸነፍ ተገደዋል፤ ከወልቂጤ፣ መቻል አዳማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስተናግደው ነጥብ ለመጣል ተገደዋል፤ ይህንን የትኩረት ማነስ ችግርም ሊቀረፍ የሚገባው ሌላው የቡድኑ ድክመት ነው።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ነጥብ የተጋሩት መድኖች በስድስት ነጥቦች አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ደረጃቸው ለማሻሻልም ሀምበሪቾን ይገጥማሉ። መድኖች እንደተጋጣምያቸው ሁሉ የማጥቃት ጥንካርያቸው ደረት የሚያስነፋ አይደለም፤ ቡድኑ ከአራት ተከታታይ ጎል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለሱ እንደ በጎ የሚታይ ቢሆንም በፈጠራ ያለው የተገደበ አቅም ግን አሁንም የግብ ድርቁ ዋና መነሻ ምክንያት ነው። አሰልጣኙም ይህንን የቡድኑ መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍም የግብ መገኛ አማራጮቻቸው ማስፋት ይጠበቅባቸዋል፤ ቡድኑ ምንም እንኳ በውስን መልኩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ለመጫወት በሞከረበት የሀድያው ጨዋታ ላይ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም በቁጥርና በጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ሀምበሪቾዎች የበረከት ወንድሙና የኃላሸት ፍቃዱን ግልጋሎት አያገኙም፤ ቅጣት ላይ ያለው ቴድሮስ በቀለም በጨዋታው አይሰለፍም። በመድን በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ከራቀው ሀቢብ ከማል በተጨማሪ ወገኔ ገዛኸኝ በነገው ጨዋታ አይኖሩም።

በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ከኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ወጋየሁ አየለ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ጋር በመሆን በጣምራ ጨዋታውን ይመሩታል።