ሪፖርት| ንግድ ባንክ መሪነቱን አስጠበቀ

ሠላሳ ስምንት ጥፋቶችና ሦስት ቀይ ካርዶች የታዩበት ጨዋታ በኢትዮጵያ በንግድ ባንክ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ንግድ ባንኮች ባለፈው ሳምንት ሻሸመኔን ካሸነፈው ስብስብ ዮናስ ለገሰን በገናናው ረጋሳ ተክተው ጨዋታውን ሲጀምሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በአዳማ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ በረከት አማረ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ፣ ኪያር መሐመድ ፣ በፍቃዱ ዓለማየሁ እና ኤርምያስ ሹምብዛን በእስራኤል መስፍን፣ ፣ ዋሳዋ ጂኦፍ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ መሐመድ ኑርና ካኮዛ ዴሪክ ተክተው ገብተዋል።


ኢትዮጵያ ቡናዎች ባደረጓቸው ፈጣን እንቅስቃሴዎች የጀመረው ጨዋታው ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ ከኳስና ከኳስ ውጭ በሚደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ነበር የተካሄደው።

በአጋማሹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው የሩብ ዕድሎች በመፍጠር በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች ብሩክ እንዳለ ከርቀት ባደረጋት ሙከራ የመጀመርያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በ20ኛው ደቂቃም በአዲስ ግደይ አማካኝነት ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በአጋማሹ የባንክ ዋነኛ የጥቃት መሳርያ የነበረው ባሲሩ ዑመር በተከላካዮች የቦታ አያያዝ ችግር ያገኛትን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሯት አዲስ ግደይ በጥሩ ቅልጥፍና ከመረብ ጋር አዋህዷታል። ባንኮች ከግቧ በኋላም ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ፈጥረዋል፤ በተለይም ባሲሩ ዑመር ከመስመር አሻግሯት በረከት ግዛው ወደ ግብነት ያልቀየራት ዕድል ትጠቀሳለች። በሠላሳ ስድስተኛው ደቂቃም ጥረታቸው ስምሮ በባሲሩ ዑመር አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ተጫዋቹ ከሱሌማን ሀሚድ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ሳጥን የገባውን ኳስ በመምታት ነበር ያስቆጠረው። በዚ ሂደትም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የመከላከል ችግር ተስተውሏል።

በአጋማሹ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ በጀመሩበት የጨዋታ ፍጥነት መቀጠል ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጋማሹ የፈጠሯቸው ዕድሎች ጥቂት ነበሩ።
ከታዩ ሙከራዎችም ካኮዛ ዳሪክ፤ ኃይለሚካኤል ያሻማውን ኳስ በጥሩ መንገድ አብርዶ መቶት ኢላማውን ያልጠበቀው ኳስ ነበር። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃም በካኮዛ ዴሪክ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ተስፋቸውን አለምልመው ወደ ዕረፍት አምርተዋል፤ ካኮዛ ዴሪክ፤  መሐመድ ኑር ባልተመቻቸ ሁኔታ ሆኖ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አዟዟር ግሩም ግብ አስቆጥሮ ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።

ቡናማዎቹ ባደረጓቸው ሙከራዎች የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የጠሩ የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር።

በቡናዎቹ በኩል አንተነህ ተፈራ ከተከላካዮች ጀርባ ሾልኮ በመሮጥ ያደረገው ሙከራና ካኮዛ ዴሪክ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ በደረቱ አብርዶ የሞከረው ሙከራ ይጠቀሳሉ። ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንገድ ያለቀላቸው ሙከራዎች የሞከሩት ንግድ ባንኮችም የኢትዮጵያ ቡናው ግን ጠባቂ እስራኤል መስፍን ጥረት ባይታከልበት የግብ መጠናቸው ከፍ የሚያደርጉባቸው ዕድሎች ፈጥረው ነበር።

ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች መካከል ኪቲካ ጅማ የቡና ተከላካዮች የኦፍሳይድ አጠባበቅ ችግር ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በእስራኤል መስፍን ቅልጥፍ ወደ ግብነት ያልተቀየረው ሙከራና በተመሳሳይ ሱሌማን ባሲሩ ዑመር በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ መቶት እስራኤል መስፍን ጥረት ወደ ግብነት ያልተቀየረ አጋጣሚ በቡድኑ በኩል ከታዩ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃም በሴኮንዶች ልዩነት ሁለት ተጫዋቾች በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥተዋል፤ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወንድሜነህ ደረጄ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሱሌይማን ሀሚድ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥተዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ቡናማዎች ብሩክ በየነ፣ አንተነህ ተፈራና ካኮዛ ዴሪክ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ብሩክ በየነ ጫላ ተሺታ ከመስመር ያሻረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ የተሻለች ለግብ የቀረበች ነበረች። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎችም ተቀይሮ የገባው ሲሞን ፒተር በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል።

ጨዋታው ሁለት ለአንድ መጠናቀቁ ተከትሎ ንግድ ባንክ ወደ ሊጉ መሪነት ሲመለስ ቡና አምስተኛ ተከታታይ ድል አልባ ጉዞውን ቀጥሏል።


ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ያገኙዋቸውን ዕድሎች መጠቀም እንዳልቻሉና የግብ መጠኑ ከዚ በላይ ከፍ ማለት ይችል እንደነበር ከገለፁ በኋላ ቡድኑ በመጨረሻው ደቂቃዎች የታየበት የመረጋጋት ችግር እንደሚቀርፉ ተናግረዋል። የቡናው አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች በበኩላቸው ጨዋታው የመጀመርያው አጋማሽ እንቅስቃሴ እንደወሰነው ገልፀው ተጋጣሚያቸው ጥቂት ዕድሎች አግኝቶ እነሱን በመጠቀም ጨዋታው አሸንፎ እንደወጣ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ ከተጋጣሚው በርቀት የተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳደረገ ጠቅሰዋል።