ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር ድል አድርገዋል

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሦስት የከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ ጨዋታዎች ሲደረጉ ወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር ድል ሲቀናቸው ኮልፌ ቀራኒዮ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ነጥብ ተጋርተዋል።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኮልፌ ከራኒዮ ክ/ከተማን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ አገናኝቷል። በኮልፌ ቀራኒዮ በኩል ጥሩ የሚባል ፍሰት ያለው የኳስ ቅብብል ተመልክተናል። በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በኩል ደከም ያለ አጨዋወት የተመለከትንበት እና ተደጋጋሚ የኳስ መቆራረጥ በአጋማሹ ታይቷል። በ20ኛው ደቂቃ ኮልፌ ቀራኒዮ ወደ ፊት በመሄድ በቃለጌታ ምትኩ አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኮልፌ ቀራኒዮ በተደጋጋሚ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር የቀረቡ ቢሆንም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸዋል። በ32ኛ ደቂቃ የኮልፌ ቀራኒዮ ተጫዋች እና የግቧ ባለቤት ቃለጌታ ምትኩ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ማስቆጠር ሳይችል የቀረበት አጋጣሚ ይታወሳል።

ከእረፍት መልስ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተነቃቁበት እና ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉበት አጋማሽ ሆኗል። በአንፃሩ ኮልፌ ቀራኒዮ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቅዘው የታዩበት አጋማሽ ሆኗል። በ57ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ከኮልፌ ቀራኒዮ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የተገኘውን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል አጨዋወት እና ግብ ላለማስተናገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የአንድ ቡድን የበላይነት የታየበት የዕለቱ የሁለተኛ ጨዋታ ወልድያን ከይርጋጨፌ ቡና አገናኝቷል። በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃ ይረጋጨፌ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። ሆኖም በ15ኛው ደቂቃ ወልድያ በጥሩ ቅብብል ከቢኒያም ላንቃሞ የተሻገረለትን ኳስ በድሩ ኑርሁሰን በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሯል። ቀጥሎም ወልድያዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የይርጋጨፌን ግብ ሲፈትሹ ቆይተዋል። በአንፃሩ ይረጋጨፌ ቡና ቀዝቅዘው ታይተዋል። መደበኛው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ የወልድያ ተጫዋች የሆነው ቢንያም ላንቃሞ በግሩም ቅብብል ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ወልድያ የበላይነቱን ማስቀጠል የቻለበት አጋማሽ ሆኗል። በ53ኛው ደቂቃ በወልድያ በኩል ተቀይሮ የገባው ፀጋ ማቲዮስ ከመስመር በግል ብቃቱ ወደ ግብ በመሄድ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ይርጋጨፌ ቡና የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። በ87ኛው ደቂቃ የወልድያው ወንድማገኝ ኪራ በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ የይርጋጨፌ ቡናን ግብ ጠባቂ እና ተከላካይን በማታለል በድንቅ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በወልዲያ 4-0 አሸናፊነት ሲቋጭ ቡድኑ ነጥቡን 11 በማድረስ ወደላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል መጠጋት ችሏል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር እና ቤንችማጂ ቡና አገናኝቷል። ካለፈው አሰላለፍ የአራት ተጫዋች ለውጥ አርጎ የገባው ጅማ አባ ጅፋር አጭር እና ረጅም ቅብብል በመቀላቀል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ቤንች ማጂ ቡና ኳስን በመቆጣጠር እና በበዛ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አርገዋል። ጨዋታው ከተጀመረ በ15ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡና በወንድማገኝ ኪራ አማካኝነት ግልፅ የግብ እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ26ኛው ደቂቃ ወንድማገኝ ኪራ ዳግም ከፍተኛ የመግባት ዕድል ያለው የግብ ዕድል አግኝቶ ወደ ግብ መቀየር ተስኖታል። ከሙከራው በኋላ ጅማ አባ ጅፋር ይበልጥ ተነቃቅተው ጥንቃቄም ጨምረው በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። ጨዋታው በማጓጓት እና እልህ በተሞላበት መልኩ ቀጥሎ አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጅማ አባ ጅፋር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ጥሩ ለመጫወት የሞከሩበትን አጋማሽ ተመልክተናል። በአንፃሩ ቤንች ማጂ ቡና ከመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ ቀዝቀዝ ብለው ታይተዋል። በ54ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋር ያገኘውን ቅጣት ምት ጌታቸው ተፈሪ ያሻገረውን ኳስ ፊሊሞን ገ/ፃድቅ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ይበልጥ ጫና የበዛበት እና ውጥረት የታየበት መሆን ችሏል። ቤንች ማጂ ቡና ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የጅማ አባ ጅፋር የተከላካይ ክፍልን ማለፍ ተስኗቸው ጨዋታው መጠናቀቅ ችሏል።