ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን የድል ረሃቡን አስታግሷል

በምሽቱ መርሐግብር መድኖች  ሀምበሪቾን 2-0 በመርታት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀምበሪቾ እና ኢትዮጵያ መድን ሲገናኙ ሀምበሪቾዎች በሰባተኛው ሣምንት በወልቂጤ ከተማ 1-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ምንታምር መለሰ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ማናዬ ፋንቱ በፖሉማ ፖጁ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና በዳግም በቀለ ተተክተው ገብተዋል። በተመሳሳይ ሣምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1-1 በተለያዩት መድኖች በኩልም የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። በዚህም አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ዮናስ ገረመው እና አዲስ ተስፋዬ በተካልኝ ደጀኔ ፣ አሚር ሙደሲር እና ወገኔ ገዛኸኝ ተተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ይደረግበት እንጂ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እና አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያልተደረገበት ነበር። የተሻለው የግብ ሙከራም 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የሀምበሪቾው ኤፍሬም ዘካሪያስ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 52ኛው ደቂቃ ላይ በሀምበሪቾዎች አማካኝነት ሲደረግ አቤል ከበደ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ አብዱልሰላም የሱፍ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በቀላሉ ይዞታል።

ኢትዮጵያ መድኖች በሁለተኛው አጋማሽ ሙሴ ከበላን እና ያሬድ ዳርዛን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።

በዚህም 64ኛው ደቂቃ ላይ ኦሊሴማ ቺኔዱ ባመቻቸለት ኳስ ያሬድ ዳርዛ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ሙሴ ከበላም ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።

በሚያገኟቸው ኳሶች በፍጥነት ከራሳቸው የግብ ክልል በመውጣት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት መድኖች 72ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል። አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አጥቂው ቹኩዌሜካ ጎድሰን ሳያገኘው ቢቀርም ከኋላ የነበረው ያሬድ ዳርዛ በደረሰው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል።

ጨዋታው 80ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በመድኖች አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። በቀኝ መስመር ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ያገኘው ቹኩዌሜካ ጎድሰን በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የሀምበሪቾ ተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ መዘናጋት ተጨምሮበት ግብ ሆኗል። ግብ ከማስተናገዳቸው በፊት ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲጥሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎችም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በድጋሚ በመነሳሳት ፈጣን እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላም በተሻለ የራስ መተማመን የቀጠሉት መድኖች 90ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። አቡበከር ወንድሙ በግንባሩ ገጭቶ ለማሻገር የሞከረውን ኳስ ተከላካዩ ዲንክ ኪያር ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ያሬድ ዳርዛ የግብ ጠባቂውን ምንታምር መለሰ መውጣት ተመልክቶ ከሳጥን ውጪ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለገብረመድኅን ኃይሌ ቡድን ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ሙሉ አቅማቸውን ማጥቃት ላይ ያደረገ እንቅስቃሴ ለማድረግ መግባታቸውን ጠቁመው ያሳኩት ድልም ለቀጣይ ጨዋታ መነሻ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል። የሀምበሪቾው አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በበኩላቸው የተጫዋቾች ጉዳት እና በሙሉ ደቂቃ የመጫወት አቅም ጉዳይ ችግር እንደሆነባቸው ጠቁመው በተከታታይ ጨዋታዎች ባለቀ ደቂቃ ግብ እያስተናገዱበት ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠር መቸገራቸውን ተናግረዋል። አሰልጣኙ አክለውም ልምድ ያለው ተጫዋች በቡድናቸው አለመኖሩን እና “የተጫዋች ጥራትም እግርኳስ ላይ ግድ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።