መረጃዎች | 32ኛ የጨዋታ ቀን

ስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይገባደዳል ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

በተለያየ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ 09:00 ላይ ይከናወናል።

ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ፋሲል ከነማን አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ አስራ አንድ ማድረስ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ከሦስት ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ሦስት ነጥብ ለማስቀጠል ሲዳማን ይገጥማሉ። የጦና ንቦቹ በመጨረሻው ሳምንት ላይ ያሳዩት ጨዋታ የመቆጣጠርና የግብ ዕድሎች የመጠቀም ብልጫ ጨዋታውን አሸንፈው እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በተለይም ከዚ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ችግር የነበረው የግብ ማስቆጠር ችግር ጠንካራውን የፋሲል ከነማ ተከላካይ ክፍል በገጠሙበት ጨዋታ በውስን መልኩ ፈተዋል፤ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለት አቻ ከተለያየበት ጨዋታ ውጭ በአንድ ጨዋታ ከሁለት ጎል በላይ ያስቆጠረበት አጋጣሚ አልነበረም። በመጨረሻው ጨዋታ ግን የማጥቃት ክፍሉ ጥሩ ተንቀሳቅሶ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከአንድ ግብ በላይ በማስቆጠር አሸንፎ ወጥቷል፤ በማጥቃቱ ላይ የታየው ጥሩ መሻሻል ማስቀጠልም ቀጣዩ ስራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ወላይታ ድቻዎች በሁለት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረ፤ በሦስት አጋጣሚዎች ደግሞ ከአንድ ግብ በላይ ያላስተናገደ ከንግድ ባንክ ጋር በጋራ ጥቂት ግቦች የተቆጠረበት ጠጣር የመከላከል ክፍላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠላቸውም ሌላው በቡድኑ የሚጠቀስ በጎ ጎን ነው።

በአምስት ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በዚህ ጨዋታ ካሸነፉ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል አለ፤ ይህንን ዕድል ለመጠቀምም ከወላይታ ድቻ ጋር ብርቱ ፍልምያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሲዳማ ቡናዎች ሻሸመኔ ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት የሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል፤ ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱ ብቻ በማሳካት በደካማ ወቅታዊ አቋም ይገኛል። ቡድኑ ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች በዘለለም ትልቅ የግብ ማስቆጠር ችግር አለበት፤ በሰባት ጨዋታዎች አራት ግቦች በማስቆጠርም ከሌሎች አራት ክለቦች ጋር ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ከዛ በተጨማሪም በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻለም። ይህንን መጥፎ የግብ ማስቆጠር ክብረ ወሰን ለመግታትም በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገደው የተከላካይ ክፍል የሚያደርገው ፍልምያ በበላይነት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።

በወላይታ ድቻ በኩል ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከነበሩት ባዬ ገዛኸኝ እና መልካም ቦጋለ ውጭ የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና የለም፤ በሲዳማ ቡና በኩልም ደስታ ዮሐንስ በጉዳት ምክንያት አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 18 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ዘጠኝ ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 27 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 9 ፣ ሲዳማ ቡና 18 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል ዳኝነት፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሲራጅ ኑርበገን ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ከሽንፈት ወደ ድል ለመመለስ የሚያልሙ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ስድስት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በአንድ ነጥብ የሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች ነጥባቸውን ከፍ ለማድረግ አዳማን ይገጥማሉ። ሻሸመኔዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ውስን የአጨዋወት ለውጥ አድርገዋል፤ ንግድ ባንክን በገጠሙበት ጨዋታም ይህን ለውጥ ተስተውሏል። በጨዋታው የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ለመከተል የሞከሩት ሻሸመኔዎች በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣምያቸው ጥቃት በተገቢው መንገድ መመከት ችለው ነበር፤ በጨዋታም ምንም እንኳ ሽንፈት ቢያስተናግዱም ጠንካራውን ባንክ የገጠሙበት አጨዋወት መንገድ ግን መጥፎ አልነበረም። ከቡድኑ ጋር ሦስተኛ ጨዋታቸው ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ዘማርያም አሁንም የሚገጥሙት ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን እንደመሆኑ ባለፈው ሳምንት የተጠቀሙበትን መከላከል ላይ ያመዘነና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚሞክር አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።

ሦስት ድል፣ ሦስት የአቻና አንድ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማዎች በመጨረሻው ሳምንት በመቻል ከገጠማቸው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ለማገገም በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙትን ሻሸመኔዎች ይገጥማሉ። አዳማዎች በፈጣን ተጫዋቾች የተገነባ ስል የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን ነው፤ ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠራቸውም የዚ አንዱ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስተናገዱ ሦስት ክለቦች ውስጥ አንዱ መግጠማቸውን ሲታይ ፈተናው ቀላል ቢመስልም ተጋጣሚያቸው በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ያሳየው ጥሩ የመከላከል መሻሻል ግን መዘንጋት የለበትም። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ ጥቅጥቅ ብሎ፣ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ የሚከላከል ቡድን እንደ መግጠሙ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሊገጥመው የሚችለውን ፈተና ለመወጣት ተጨማሪ የግብ ማግኛ መንገዶች ማበጀት ይኖርበታል።

ሻሸመኔዎሽ አሁንም የያሬድ ዳዊትን ግልጋሎት አያገኙም፤ በአዳማ በኩልም አድናን ረሻድ የነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያመልጠው ሲሆን መጠነኛ ጉዳት ላይ የነበረው ቦና ዓሊ ግን ለነገው ጨዋታ የሚደርስ ይሆናል።

ነገ ከ2000 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 2 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው በሁለቱም አጋጣሚዎች አዳማ ከተማ (1-0 እና 2-0) ማሸነፍ ችሏል።

አዲሱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና አዲሱ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰ በረዳትነት እያሱ ፈንቴ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።