ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው የመስመር ተከላካይ ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ተረጋግጧል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና በድሬደዋ ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ የመስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ የጉልበት ህመም አስተናግዶ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት ተቀይሮ ከሜዳ ሲወጣ ተስተውሏል።
ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በውዳሴ ዲያግኖስቲክስ የህክምና ምርመራውን ያደረገው ደስታ ዮሐንስ ህመሙ እንደተፈራው እንዳልሆነ እና ምንም ዓይነት የጅማት መበጠስ እንዳላጋጠመው የተነገረው ሲሆን ለአራት አልያም ለአምስት ሳምንታት ዕረፍት በማድረግ ወደ ልምምድ እንደሚመለስ በባለሙያዎች ተነግሮታል።