ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

ሲዳማ ቡና 4ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ወላይታ ድቻን በመርታት በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

ወላይታ ድቻ በፋሲል ላይ ድል የተቀናጀው ስብስቡን ሳይለውጥ ሲቀርብ በድሬዳዋ ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በሦስቱ ላይ ቅያሪን አድርገዋል። መክብብ ደገፉ ፣ ደስታ ዮሐንስ እና ሚካኤል ኪፕሮቭን በመሐመድ ሙንታሪ ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና ሙሉቀን አዲሱ ተክተዋቸዋል።


በፀሐያማ የዓየር ሁኔታ ውስጥ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከፍ ባለ ተነሳሽነት የጀመሩበት ይሁን እንጂ ወላይታ ድቻዎች በሂደት በማጥቃቱ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ሻል ያለ ነበር። አማካይ ክፍሉን ከሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች ጋር በማቀናጀት በጥልቀት ወደ ውስጥ ፈጠን ባለ እንቅሰቃሴ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ኳስን በሚያገኙበት ወቅት ቢኒያም ፍቅሬን ባማከለ መልሶ ማጥቃትን የሚጠቀሙት የጦና ንቦቹ ከጎል ጋር ለመገናኘት ከተጋጣሚያቸው አንፃራዊ ብልጫ ይዘዋል። ድቻዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የተገኘን የቅጣት ምት ፍፁም ግርማ ሲያሻማ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ሲተፋው አንተነህ ጉግሳ እግሩ ስር የደረሰችውን ኳስ መቶ ከግቡ አግዳሚ በላይ ሰዷታል።

ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት ፈጣን መልሶ ማጥቃት ላይ በይበልጥ መሳተፋቸውን የቀጠሉት ድቻዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ የግብ ዕድልን ፈጥረዋል። ብዙአየው ሰይፈ ወደ ግራ አቅጣጫ የሰጠውን ኳስ ቢኒያም ፍቅሬ ምቹ ባልሆነው ግራ እግሩ ወደ ግብ ሞክሮ ሙንታሪ በጥሩ ቅልጥፍና ይዞበታል። ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ባለ ቅብብል ይድረሱ እንጂ ከአፈፃፀም አኳያ ውስንነቶች የነበሩባቸው ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያ ሙከራቸው ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። 20ኛው ደቂቃ ከማዕዘን በዛብህ እና ፍቅረየሱስ ተቀባብለው ያስጀመሩትን ኳስ በዛብህ ወደ ግብ መቶ በተከላካዮች ሲመለስ ዳግም ኳሱን ያገኘው ፍቅረየሱስ አሻምቶ ሀብታሙ ገዛኸኝ በጥሩ መቀስ ምት ማራኪ ጎል ከመረብ አዋህዷል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በመስመር እና ከቆሙ ኳሶች ወደ አቻነት ለመሸጋገር ወላይታ ድቻዎች ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም አጋማሹ በሲዳማ ቡና 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ቡድኖቹ የተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ሲዳማዎቸ ጉዳት ባስተናገዱት ሀብታሙ እና ይገዙ ምትክ ሚካኤል ኬፕሮቭ እና ቡልቻ ሹራን ድቻዎች በአንፃሩ ዘላለም አባተን በብስራት በቀለ ከተኩ በኋላ ነበር ጨዋታው የቀጠለው። አጋማሹ ተጀምሮ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ብቻ እንደ ተቆጠረ ሲዳማ ቡና የግብ መጠናቸውን ያሳደገች ግብ አግኝተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የድቻ የማዕዘን መምቻ አካባቢ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጋናዊው ሚካኤል ኪፕሮቭ ወደ ውስጥ ሲያሻማ በዛብህ መለዮ በግንባር ገጭቶ በቀድሞው ክለቡ ላይ ጎል አስቆጥሯል። ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ በመጠኑ ወረድ ያለ እንቅስቃሴዎች በበዙበት በዚህኛው አጋማሽ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አከታትለው ወላይቻ ድቻዎች ካደረጉ በኋላ ወደ ጨዋታ የምትመልሳቸውን ግብ አግኝተዋል።

71ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ ብስራት ጨርፎለት ዮናታን ኤልያስ ሁለቴ ገፋ አድርጎ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ኳሷን መረብ ላይ አስቀምጧታል። በይበልጥ ለማጥቃት ትኩረት ሰጥተው ለኋላ መስመራቸው ሽፋን በመስጠቱ ድክመቶች የተንፀባረቀባቸው ወላይታ ድቻዎች ከሦስት ደቂቃዎች መልስ ጎል አስተናግደዋል። 74ኛው ደቂቃ ከራስ ሜዳ ኳስን እየገፋ ወደ ሳጥን የደረሰው ሚካኤል ኪፕሮቭ የተከላካይ እና የግብ የጠባቂ ስህተት አግዞት ቆንጆ ሦስተኛ ጎል በግሩም አጨራረስ አስቆጥሯል። ተቀይሮ ከገባ በኋላ በቀኝ በኩል ለድቻ ተከላካዮች ራስ ምታት ሆኖ የቀረበው ቡልቻ ሹራ ካደረጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ ጎል ከመረብ አሳርፏል። 86ኛው ደቂቃ ተከላካዮችን አልፎ አንድ ሁለት ከኪፕሮቭ ጋር የተጫወተው ቡልቻ ቢኒያም ገነቱ መረብ ላይ በማራኪ አጨራረስ አራተኛ ጎልን ለሲዳማ አክሏል ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመምጣት ድቻዎች በቢኒያም እና አብነት ቀዳዳ ፍለጋን ቢጀምሩም ጨዋታው በሲዳማ ቡና የ4ለ1 አሸናፊነት በመጨረሻም ተቋጭቷል። ድሉም ሲዳማን ከሦስት ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ወደ ድል አድራጊነት ያሸጋገረ ሆኗል።


ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በጨዋታው ጥሩ እንዳልሆኑ እና በዚህም ጎል እንደተቆጠረባቸው አውስተው ደካማ እንቅስቃሴን እስከ አሁን ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንፃር ማድረጋቸው እና በመከላከሉ ከነበራቸው ድክመት ችግሩ መፈጠሩን ይህንንም በቀጣይ እንደሚቀርፉም ጭምር ተናግረዋል። የሲዳማ ቡናው አቻቸው አረጋዊ ወንድሙ በበኩላቸው ፈጥነው ጎል ለማስቆጠር አቅደው እንዲሁም የተጋጣሚ ተጫዋቾችን በማስቆሙም ረገድ አስበው የገቡትን እቅድ ማሳካት መቻላቸውን ጠቅሰው በተሰሩ የልምምድ ስራዎች የተገኘ ድል መሆኑንም ጠቁመዋል።