ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከ36 ወራት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል

የ7ተኛ ሳምንት ተስተካካዩ የሸገር ደርቢ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና የ1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገደበት የንግድ ባንኩ ጨዋታ በአምስቱ ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርጓል። እስራኤል መስፍን ፣ ወንድሜነህ ደረጀ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አንተነህ ተፈራ እና ካኮዛ ዴሪክ አርፈው በረከት አማረ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ በፍቃዱ ዓለማየሁ ፣ መስፍን ታፈሰ እና አብዱልከሪም ወርቁ በምትኩ ወደ ቋሚነት ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀዋሳ ላይ ድል የቀናው ስብስቡን  ዛሬም ወደ ሜዳ ይዞ ገብቷል።

ከፍ ባለ የራስ መተማመን ጨዋታውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያውን አስር ደቂቃ በወሰዱት ብልጫ ከአማካይ ክፍሉ በሚደረግ ንክኪ አቤል ያለውን ትኩረት ባደረጉ ሰንጣቂ ኳሶች አልያም ወደ ቀኝ ባዘነበሉ እንቅስቃሴዎች የጥልቅ አጨዋወት ከጎል ጋር ለመገናኘት ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ከራስ ሜዳ አማኑኤል ተርፉ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አቤል ያለው በጥሩ ብልጠት ለቢኒያም በላይ ሰጥቶት ተጫዋቹ ባልተመቻቸ እግሩ ወደ ጎል ቢመታም ኳሷ የግቡን የግራ ቋሚ ጨርፋ ወጥታለች። የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ወስደው አቤል ያለው ላይ አነጣጥረው ጨዋታውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያ ሙከራ በኋላ ማለትም ከአንድ ደቂቃ መልስ ሔኖክ አዱኛ በረጅሙ ከቀኝ ወደ ቡና የተከላካይ ክፍል ያሻገረውን ኳስ አቤል ከቀኝ ወደ ሳጥን ገፋ አድርጎ ወደ ግብ ሲመታ በረከት አማረ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።

በጊዜ ወደ ጨዋታ ለመግባት ተቸግረው የቆዩት እና ቀስ በቀስ የጊዮርጊስን የቅብብል ስህተት እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች ቀዳዳ መፈለግን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ጎል በላካት እና ባሕሩ ነጋሽ ወደ ውጪ ባስወጣት ኳስ ወደ ግብ ደርሰዋል ቡድኑ ከደቂቃ በኋላም ሌላ ጥራት ያለው አጋጣሚን ከቆመ ኳስ አግኝተዋል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ብሩክ ያሻማው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ጫላ እግር ስር ደርሳ ተጫዋቹ ያመቻቸውን አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በሚገርም ብቃት ኳሷን አውጥቷታል። ከጨዋታው አካፋይ ሰዓቶች መልስ ቀዝቀዝ ባሉ እንቅስቃሴዎች ጨዋታው ቀጥሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች በድግግሞሽ ወደ ሳጥኑ በቅብብል ሲደርሱ ብንመለከትም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ግን የጊዮርጊስን የመከላከል አደረጃጀት ማለፍ ተስኗቸው ያስተዋልን ሲሆን ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ከቀኝ ወደ ውስጥ በሚደረጉ እና አቤልን ያነጣጠሩ አጨዋወቶችን ቡድኖቹ ቢከተሉም ከሙከራዎች አኳያ የሳሳው አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ዝግ ባሉ እንቅስቃሴዎች ጅምሩን ቢያደርግም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በንፅፅር ሻል ብለው የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከቆመ ኳስ ግብ አግኝተዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ የሜዳው ክፍል የተገኘውን የቅጣት ምት ዋሳዋ ጂኦፎሪ በቀጥታ ወደ ግብ ሲያሻማ ፍሪምፓንግ ሜንሱ ማውጣት የተሳነውን ኳስ በንክኪዎች ያገኘው ጫላ ተሺታ ጎል አድርጓት ቡናን ቀዳሚ አድርጓል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ዳዊት ተፈራ እና ናትናኤል ዘለቀን በፍሪምፖንግ ኩዋሜ እና አማኑኤል ኤርቦ የተኩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አቤል እና ተገኑን ተጠቅመው ጎልን ለማስቆጠር የሞከሩበትን ሂደት ብናስተውልም በቀላሉ የቡናን ተከላካይ በማለፉ ረገድ ግን አልታደሉም።

ኳስን ሲያገኙ በፈጣን ሽግግር ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉ የነበሩት ቡናማዎቹ 62ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ሙከራን አድርገዋል። ብሩክ በረጅሙ ለመሐመድኑር ሰጥቶት አጥቂው ነፃ ቦታ ለነበረው መስፍን ታፈሰ አቀብሎት ተጫዋቹ በቀላሉ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን ወደ ላይ ሰቅሏታል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጨረሻውን አስር ደቂቃ ወደ አቻነት ለመምጣት በረጃጅም ኳሶች እና በሁለቱ መስመሮች በኩል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት ከጎል ጋር ለመገናኘት ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተለይም 93ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ኤርቦ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ከግቡ ጋር ተገናኝቶ በተከላካይ እና በግብ ጠባቂው ርብርብ ልትወጣ የቻለችው ኳስ የምታስቆጨዋ የቡድኑ የመጨረሻ ዕድል ሆና ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና በ2013 (ከ36 ወራት በፊት) በመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በአቡበከር ናስር ሀትሪክ ታግዞ 3ለ2 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ማለትም ከሦስት ዓመታት ቆይታ መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ችሏል። የዛሬውን ውጤት ተከትሎ ቡናማዎቹ ስድስት ደረጃዎችን በማሻሻል ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡም ችለዋል።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ክፍተት እንደነበር ገልፀው። ካደረጉት እንቅስቃሴ አንፃር ውጤቱ ቡድናቸውን እንደማይገልፀው ጠቅሰው መሸነፍ አይገባንም ውጤቱን ግን እቀበለዋለሁ ሲሉ የተደመጡ ሲሆን መጫወት ያለባቸውን እንዳልተጫወቱ ነገር ግን በእግር ኳስ የሚያጋጥመው እንደገጠማቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡናው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው በመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃዎች ተጋጣሚያቸው የተሻለ እንደነበር ጠቁመው ጥንቃቄን ይዘው ገብተው ወደ ጨዋታ በመግባታቸው ጎል አስቆጥረው ማሸነፍ መቻላቸውን ገልፀው በመከላከሉ ጥሩ በመሆናቸው አሸንፈው እንደወጡ እና ደስ የሚል ስሜት እንደተሰማቸው እና በውጤቱም ደጋፊዎቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።