ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በምድብ  “ሀ” 9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ንብ እና ቤንች ማጂ ቡና ድል ሲቀናቸው ተጠባቂው የአዲስ አበባ ከተማ እና ነቀምቴ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ረፋድ 3:30 ሲል የጀመረው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ቀን መርሀ ግብር ያለፈው ጨዋታቸውን ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት ንብን ከሀላባ  ከተማ አገናኝቷል። ጥቂት የግብ እድል የተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀላባ ከተማ በአንፃሩ ተሽለው የተገኘበት አጋማሽ ሆኖ አልፏል። ንብ ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅሞ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ሆኖም ኳሶቹ ለታቀደላው ኢላማ መድረስ ሳይችሉ ሲበላሹ ተስተውሏል። ሀላባ ከተማም ጥቂት የሚባል ለግብ ቀርበው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ13ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማ ወደፊት በመሄድ ሳሙኤል ተስፋዬ ከመስመር ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ አሸናፊ በቀለ ግልፅ የሆነ የግብ እድል ኳሱን በማንጠር ኢላማውን ሳይጠብቅ መውጣት ችሏል። በ45ኛው ደቂቃ የሀላባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ሰለሞን ያለው በተመሳሳይ ከቀኝ በኩል ወደ ግብ የተመታውን ኳስ የንብ ግብ ጠባቂ ሳይነካው ቀርቶ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰውን ኳስ ምትኩ ባንዳ በግንባር ወደ ግብ ሞክሮት ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወቷል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የመለከትንበት ሆኗል። ንብ ተሻሽሎ የገባበት እና ውጤታማ የሆነ ፈጣን መልሶ ማጥቃት ውጤታማ ለመሆን ሲጥሩ የተመለከትንበት ሲሆን ሀላባ ከተማም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። በ65ኛው ደቂቃ ላይ የንብ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ሰለሞን ላይ የሀላባ ተከላካይ የሆነው ኪሩቤል ማርቆስ በሰራው ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ኪዳኔ አሰፋ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀላባ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አርገዋል። በ78ኛው ደቂቃ ላይ የንብ ተከላካይ የሆነው አሌክስ ተሰማ የተሳሳተውን ኳስ ምትኩ ባንዳ ያገኘውን ግልፅ የግብ እድል በመሳት አቻ የሚሆኑበትን እድል አባክኗል። ጨዋታውም በዚው ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀላባ ከተማ ግብ ጠባቂው ሀብታሙ ከድር ከእለቱ ዳኛ ጋር ባደረገው ሰጣገባ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።

በመቀጠል በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማን ከነቀምቴ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማ ጥንቃቄን አብዝቶ በመምረጥ ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ ነቀምቴዎች ከተማ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህንን ተከትሎ በ3ኛው ደቂቃ ምኞት በፍቃዱ ለኢብሳ በፍቃዱ ያቀበለውን ኳስ በግንባር ለማስቆጠር ለጥቂት ወደ ውጪ መውጣት ችሏል። ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ አጨዋወት ያገኘውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባር ማስቆጠር ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማ ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም በመነቃቃት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ የሆነ ጥረት አድርገዋል። በዚህም 52ኛው ደቂቃ ከተቃራኒ የግብ ክልል ላይ ያገኘውን ኳስ ዝናቡ ዳመና ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ በነቀምት ከተማ ግብ ጠባቂ በመዘናጋቱ ኳሱ ወደ ግብ ተቀይሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ አጨዋወት አስመልክተውን ጨዋታውም በዚው ውጤት መጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ እስካሁን ሽንፈት ያልገጠመው አዲስ አበባ ከተማ ነገ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስከሚጫወት የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

ቀን 7:30 ላይ በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ከሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ተገናኝቶ 2-0 አሸንፏል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ቤንችማጂ ቡና ኳስን መሠረት አድርገው በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ ተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንፃሩ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ኳስን ወደፊት ለመሄድ ምንም ፍላጎት ባለማሳየት ብዙ ጊዜያቸውን በራሳቸው የግብ ክልል ሰብሰብ ብለው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በጨዋታው የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ተጫዋቾች ሀይል በመጠቀም የቤንች ማጂ ቡናን ጫና ለመከላከል ሙከራ አድርገዋል። በ39ኛው የቤንችማጂ ቡና ተጫዋች የሆነው ብሩክ ወልዱ የኮልፌ ቀራኒዮው ወሰኑ አሊ ላይ ጥፋት በመስራቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።  መደበኛው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ የቤንችማጂ ቡና ተጫዋች ዳግም ሰለሞን ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ አጋማሹ በቤንችማጂ ቡና መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ አጨዋወት ተጫውተዋል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ የወሰደውን የተጫዋች ብልጫ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስለውሏል። ሆኖም የቤንችማጂ ቡናን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በ62ኛው ደቂቃ በድጋሚ ከኮልፌ ክ/ከተማ የግብ ክልል ትንሽ ራቅ ብሎ የቤንችማጂ ቡና ተጫዋች የሆነው ዳግም ሰለሞን ላይ የተሰራውን ጥፋት ራሱ ዳግም ሰለሞን ከርቀት አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቤንች ማጂ ቡና ነቀምቴ ከተማን በመብለጥ ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።