ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ነጌሌ አርሲ ወደ ድል ሲመለስ ሸገርም አሸንፏል

ከሦስት ቀን እረፍት በኋላ በተደረገው  የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን መርሐ ግብር ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ባቱ ከተማ፣ ሸገር ከተማ እና ነጌሌ አርሲ ሦስት ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ጋሞ ጨንቻን ከባቱ ከተማ ጋር ያገናኘው የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ብዙም የግብ ሙከራዎች ሳያስመልክት በጠባብ ውጤት በባቱ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው ይህ መረሐ ግብር በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታ ቁጥጥር ደካማ እንቅሰቃሴ ያስመለከቱ ሲሆን በመፈራራት በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ባያስመለከቱም የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ቀርተው እያለ አማኑኤል ተፈራ ያገኘውን እድል ተጠቅሞ ኳስና መረብ አገናኝቶ የመጀመሪያ አጋማሽ 1-0 ባቱ ከተማ እየመራ እንዲወጣ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጋሞ ጨንቻ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት እድርጓል። ሆኖም ባቱ ከተማ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው ሲከላከሉ ተስተውለዋል። በዚህም ጨንቻዎች የተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል መግባት ተስኗቸው ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። በዚህም መሠረት ባቱ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ግብ በጠባብ ውጤት 1ለ0 አሸንፏል።

በማስከተል 8:00 ላይ በተደረገ ጨዋታ ሸገር ከተማ አዲስ ከተማ ክ/ከተማን በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። ጥሩ እንቅስቃሴ በተመለከትነው በዚህ ጨዋታ ሸገር ከተማ ከእንቅስቃሴ ብልጫ ጋር አዲስ ከተማ ክፍለከተማን ሲያንፍ የሸገር ከተማ ማሸነፊያ ግቦችን ሀይከን ዶዋሮ እና ፋሲል አስማማው አስቆጥረዋል።

ገና ጨዋታ እንደጀመረ ኳስን ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ሸገር ከተማዎች በ4ኛው ደቂቃ በመስመር በኩል አላዛር ሽመልስ ለፊት መስመር ተጫዋች ለሀይከን ዳዋሮ አሻግሮለት ኳስና መረብ አገናኝቶ 1ለዐ መምራት ችለዋል።

ሸገር ከተማ በተከታታይ በተደጋጋሚ ከባባድ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን አዲስ ከተማ ክፍለከተማ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት በሚሄዱበት ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ፋሲል አስማማው ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በበኩላቸው የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የተስተዋሉ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃ አህመድ አብዶ በእራሱ ጥረት ግብ አስቆጥሮ ወደጨዋታ እንዲመልሱ ቢያደርግም እረፍት 2ለ1 እየተመሩ ወደመልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተሻሽሎ በመግባት ለተወሰነ ደቂቃ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርጓል። ሆኖም ግን ሸገር ከተማ በመከላከል በመጫወቱ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኗቸዋል። ሸገር ከተማም በአንፃሩ አልፎ አልፎ የግብ ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ደቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው ከቦክስ ውጪ ሆኖ አክርሮ መጥቶ ባስቆጠራት ግብ ሸገር ከተማ 3 ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነጌሌ አርሲን ከቦዲቲ ከተማ አገናኝቷል። በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ የጣለው ነጌሌ አርሲ ቦዲቲ ከተማን በሰፊ በግብ ልዩነት አሸንፏል።

ነጌሌ አርሲዎች ወደአሸናፊነት ለመመለስ ጨዋታው እንደተጀመረ ጫና ፈጥሮ ኳሶችን ወደተቃራኒ ቡድን ሲያንሸራሽሩ ተመልክተናል። ከተደጋጋሚ ከግብ ሙከራ በኋላ በ7ኛው ደቂቃ ትንሳኤ ኑር ሙሉቀን ተስፋዬ ከመስመር አሻግሮለት ኳስና መረብ አገናኝቷል።

የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ነጌሌ አርሲዎች ብዙ የግብ  ሙከረዎችን አድርገዋል። ተጋጣሚው ቦዲቲ ከተማ በአንፃሩ ዛሬ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን እምብዛም የግብ ሙከራዎችን ሲያድርጉ አልተመለከትንም።

የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ በታየው ደቂቃ በዛሬው ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ የጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ሙሉቀን ተስፋዬ ከመሐል ሜዳ አከባቢ መጥቶ ኳስና መረብ አገናኝቶ የመጀመሪያ አጋማሽ ነጌሌ አርሲ 2ለ0 እየመራ መውጣት ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የግብ ሙከራዎች ያልተመለከትን ሲሆን ነጌሌ አርሲ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ በማፈግፈግ ሲከላከሉ ተስተውለዋል። ቦዲቲ ከተማም ደካማ እንቅስቃሴ ያሳየበት ሁለተኛው አርባ አምስት አስመልክተዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ቀርቶ እያለ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ታምራት ኢያሱ በግንባሩ ገጭቶ ወደግቢነት ቀይሮ ነጌሌ አርሲ የግብ ልዩነታቸውን 3 በማድረግ ሶስት ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፎ እንዲወጣ አስችሏል።

የምድብ ለ ዘጠነኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር ነገ ከ3:00 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ይከናወናሉ።