የአሰልጣኞች አስተያየት | መቻል 2-1 ሀዋሳ ከተማ

“እግር ኳስ ውስጥ እንዴት ተጫወተ አይደለም ማን አሸነፈ ነው” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

“ከክለቡ ጋር የማወራው ነገር ይኖራል” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ መቻል 2ለ1 በሆነ ውጤት ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ጨዋታው…

“እግር ኳስ ውስጥ እንዴት ተጫወተ አይደለም ማን አሸነፈ ነው ፣ ለፕሮሰሱ ብዙ አልጨነቅም አሁን ውጤቱ ላይ ነው ትኩረቴ ምክንያቱም አንተ ራስህ ማን አሸነፈ ብለህ ነው የምትፅፈው እንጂ ማን ተጫወተ አትልም ስለዚህ ያ ነው።”

በሁለቱም አጋማሾች ከግማሽ በኋላ ባሉ ደቂቃዎች ቡድኑ መቀዛቀዙ ከምን የመነጨ ነው…

“ምክንያቱም ጎሉን ከመጠበቅ ነው ፣ የሚመራ ቡድን ሁሌም ያንን የያዘውን ጎል ይዞ ነው ለማግባት የሚሄደው ፣ ተቃራኒ ቡድን ግን ያቺን ለመመለስ ሲል ከፍቶም ሁሉ ሊጫወት ይችላል እና ያ ነው የሚመስለኝ።”

ከድሉ ባሻገር እንደ አሰልጣኝ በቡድኑ ውስጥ ምን ጥንካሬ ፈጥሪያለሁ ብለው ያስባሉ…

“ጠንካራው ህብረታችን ነው። እነዚህ ልጆች አምናም ነበሩ በአብዛኛው ስለዚህ ህብረታችን ነው። ተጫዋቾች እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥብቅ ነው አንዱ ለአንዱ ያለው አመለካከት መልካም ነው ፣ አንድ ተጫዋች ቢገባም ባይገባም ብዙ ችግር የለበትም ይሄ ህብረታችን ነው የውጤቱ ሚስጥር።”

ቡድኑ ውስጥ ከሚታየው ተነሳሽነት አንፃር ስለ ዋንጫ ማሰብ ጀምሬያለሁ ማለት ይቻላል ከተጫዋቾች ስነ ልቦናም አኳያ…

“በዚህ ሰዓት ስለ ዋንጫ ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል ብዬ አስባለሁ ፣ እኛ ስለ ዋንጫ አናስብም ስለ ዕለት ጨዋታ ነው የምናስበው አሁን እኔም ሆነ ተጫዋቾቼም ከድሬዳዋ ጋር ስላለን ጨዋታ ብቻ ነው። ከዛ በኋላ ስላለው አናውቅም ስለዚህ ቀጣዩን ካሸነፍክ ቀጣይም ለማሸነፍ ነው የምትሄደው ያኔ ሂደቶቹም እየተስተካከሉ ይመጣሉ።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ብርቱ ፉክክርን አድርገው ስለ ተሸነፉበት ጨዋታ…

“የጨዋታው እንቅስቃሴ መጥፎ ባይሆንም በተደጋጋሚ ሽንፈት ትንሽ ቡድኔ ላይ የስነ ልቦና ጫና ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ጎሎች የሚገቡት በጣም ኢዚ በሆኑ መንገዶች ነው ያ ጭንቀት የፈጠረው ነገር ነው ፣ ከዛ ውጪ በተቃራኒው ደግሞ የምናገኛቸውን ፣ የምናባክናቸው ደግሞ ያን ጭንቀት ነው የሚያሳየው እና ቡድናቸን ውስጥ ምን እንዳጋጠመ ግራ ገብቶኛል ማለት እችላለሁ።”

በሁለቱም አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃ ተቀዛቅዘው እየቆዩ ወደ ጨዋታ ይገቡበት ስለነበረው ሁኔታ…

“መጀመሪያ ጎላችንን ጠብቀን ለመጫወት ነበር ያሰብነው በዛ መሐል ነው የቆሙ ኳሶችን የተጠቀሙት ፣ ከዛ በኋላ ለመመለስ ብዙ ጊዜ ባይወስድም ከዕረፍት በኋላም እኛም አስቆጥረን ወደ ጨዋታው ተመልሰን ነበር። በመጨረሻም ባደረግነው እኛም አግኝተን በሳትናቸው ተሸንፈን ልንወጣ ችለናል።”

ቡድኑን ወደ ውጤት ለመመለስ በቀጣይ ምን ማድረግ አለብኝ ብለህ ታስባለህ ምን እንጠብቅ …

“ከክለቡ ጋር የማወራው ነገር ይኖራል ብዬ ነው የምመልስልህ።