ሪፖርት | ነብሮቹ እና ፈረሠኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ምሽት ላይ የተደረገው የሀዲያ ሆሳዕና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀዲያ እና ጊዮርጊስ ሲገናኙ በ9ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ቡድኖቹ ከተጋጣሚያቸው ጋር ካደረጓቸው ጨዋታ በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥን አድርገዋል። ሀዲያ ሆሳዕና ከአዳማው ድል ሠመረ ሀፍታይን አሳርፎ በበረከት ወልደዮሐንስ ከመቻል አቻ ተለያይተው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ባህሩ ነጋሽን አሳርፈው በፋሲል ገብረሚካኤል በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ፈረሠኞቹ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ቡድኖች ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 5ኛው ደቂቃ ላይ ነብሮቹ የአጋማሹን የተሻለ ሙከራ ሲያደርጉ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን አጠገብ የመታው ኳስ በተከላካይ ጥቂት ተሸርፎ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የተጋጣሚን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ለመግባት የተቸገሩት ጊዮርጊሶች በአማኑኤል ተርፉ ፣ አቤል ያለው እና ረመዳን የሱፍ አማካኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎችም ፈታኝ አልነበሩም። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ሀዲያዎች በአንጻሩ 43ኛው ደቂቃ ላይ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ደስታ ዋሚሾ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ነብሮቹ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ መነቃቃት አሳይተው 49ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ብርሃኑ ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሳይቆጣጠረው በቀረው ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን መትቶ ፋሲል ገብረሚካኤል ሲይዝበት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሳሙኤል ዮሐንስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ግርማ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ ወጥቷል።

ከወትሮው በተለየ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተዳክመው የቀረቡት ፈረሠኞቹ በነብሮቹ ተከላካዮች እጅግ ሲፈተኑ ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴም ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ተቸግረዋል። ሆኖም 70ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል የወጣው ኳስ የተሻለው  ሙከራቸው ነበር።

በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎችም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግም በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።