ሪፖርት | ቡናማዎቹ እና ነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ቀዝቃዛ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

በ11ኛ ሣምንት ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች በ10ኛ ሳምንት ከተጋጣሚያቸው ነጥብ ሲጋሩ ከተጠቀሟቸው አሰላለፎች ለውጦችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና ከሻሸመኔ ከተማው ጨዋታ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በራምኬል ጀምስ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ብሩክ በየነ ምትክ ወንድሜነህ ደረጀ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና ከአንድ ዓመት በላይ የጉዳት ቆይታ በተመለሰው አስራት ቱንጆ ሲተኳቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው በነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ጉዳት ባስተናገደው ብሩክ ማርቆስ ምትክ ሠመረ ሀፍታይን ያስገቡበት ብቸኛ ቅያሪያቸው ሆኗል።

ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው ጨዋታ ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በማጥቃት እንቅስቃሴው ግን አልፎ አልፎ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ሸግግር ለማድረግ የሚሞክሩት ሀዲያዎች በመጠኑ የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ግን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሁለቱም ቡድኖች ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል 19ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥሮ የመሃል ተከላካዩ ዳግም ንጉሤ በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ በመንሸራተት ተደርቦ የመለሰበት በነብሮቹ በኩል 36ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ ከቅጣት ምት አሻግሮት ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው በረከት ወልደዮሐንስ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ የተሻሉ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

ጨዋታው 40ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲደረግ መስፍን ታፈሰ ከጫላ ተሽታ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ያደረገው ሙከራ በተከላካይ ተጨርፎ በግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ተይዞበታል።

ማራኪ ፉክክር በተደረገባቸው የአጋማሹ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ግብ አስቆጥረዋል። በቅድሚያም የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ አብዱልከሪም ወርቁ በውድድሩ የእስካሁን ጉዞ ምርጥ የሚባለውን ግብ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ሲችል የቡድኑ መሪነት የዘለቀው ግን ለሦስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። የነብሮቹ ፈጣን የመስመር አጥቂ  ተመስገን ብርሃኑ ከቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ አግኝቶት ከተከላካይ እና ከግብ ጠባቂ ጋር በመታገል ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ቢወስዱም ነብሮቹ በጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ሲቀርቡ 49ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ ዒላማውን ሳይጠብቅ ከወጣበት ኳስ ውጪም ሁለቱም ቡድኖች አንድም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 87ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለው ንጹህ የግብ ዕድል ሲፈጠር ተመስገን ብርሃኑ ከበየነ ባንጃ በተመቻቸለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያገኘውን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።