ሪፖርት | ነብሮቹ እና ብርቱካናማዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት የሀዲያ ሆሳዕና እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ ተገናኝተው ከአሥራ ሁለተኛ ሣምንት ጨዋታቸው ብርቱካናማዎቹ 3ለ0 በሆነ ውጤት ፈረሠኞቹን ሲረቱ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ከወላይታ ድቻ ጋር 1-1 ተለያይተው በመጡት ነብሮቹ በኩል በተደረገ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ከጨዋታ በኋላ የጨዋታ አመራሮችን በመዝለፉ የሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በተጣለበት በረከት ወልደዮሐንስ ምትክ ግርማ በቀለ ተተክቷል።

መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ትግሎች ውጪ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። ሆኖም የመጀመሪያው የጠራ የግብ ዕድል 8ኛው ደቂቃ ላይ በድሬዳዋዎች አማካኝነት ሲፈጠር ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ዒላማውን ባልጠበቀ የጭንቅላት ኳስ አባክኖታል።

ለተጋጣሚያቸው ክፍት ቦታ ላለመስጠት ጥቅጥቅ ብለው መጫወትን የመረጡት ነብሮቹ የአጋማሹን የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ 8ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ተመስገን ብርሃኑ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ መልሶበታል።


ከራሳቸው የግብ ክልል ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመውጣት ሲሞክሩ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ 22ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ አንጃው አማካኝነት ከቅጣት ምት ባደረጉት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ከወጣው ኳስ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ 28ኛው ደቂቃ ላይ በሠሩት ስህተት ግብ ሊቆጠርባቸው እጅግ ተቃርቦ ነበር። ግርማ በቀለ ከመሃል ተከላካዩ ኢያሱ ለገሠ በነጠቀው ኳስ እጅግ ወርቃማ ዕድል ቢያገኝም በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ በእግሩ መልሶበት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍታይ ከመሃል በተሰነጠቀለት ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ቢፈጠርም የመሃል ተከላካዩ እስማኤል አብዱልጋኒዩ በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

እየተቀዛቀዘ እና ይበልጥ አሰልቺ እየሆነ በሄደው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅቶ በመግባቱ በኩል ብልጫ የተወሰደባቸው ብርቱካናማዎቹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠሩ ሱራፌል ጌታቸው ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ከጨዋታው ውጤት ለማግኘት ቢታትሩም 90ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያዎች ባደረጉት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተመስገን ብርሃኑ ከማቀበል አማራጭ ጋር በሳጥኑ የግራ ክፍል እየገፋ የወሰደውን ኳስ የዕለቱ የጨዋታው ኮከብ የነበረው የመሃል ተከላካዩ እስማኤል አብዱልጋኒዩ አቋርጦበታል። ከዚህ አጋጣሚ ውጪም ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በ13 ጨዋታዎች 9ኛ የአቻ ውጤት ማስመዝገባቸው ደስተኛ እንዳላደረጋቸው በመጠቆም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያላቸው አቅም ውስን መሆኑን እና ተጫዋቾቹ ላይ ድካም ማየታቸውን ተናግረዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ በበኩላቸው በሁለቱም በኩል የመፈራራት ጨዋታ እንደነበር ገልጸው በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልነበሩ በመጠቆም ቡድኑን ከያዙ በኋላ በሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ማስመዝገባቸውን ጥሩ እንደሆነም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።