ኢትዮጵያ ቡና ቅጣት ተላልፎበታል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና ከኮልፌ ቀራንዮ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተከስቷል ባለው ድርጊት የዲሲፕሊን ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ የውድድር አመራር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በ16/04/2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ዋንጫ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ጨዋታ ታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲኘሊን ሪፖርት ከመረመረ በኃላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ከ ኮልፌ ቀራኒዬ እግር ኳስ ክለብ ጋር 3ኛውን ዙር የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በ14/04/2016 ዓ.ም በ9፡30 ሰዓት ባደረጉት ጨዋታ ወቅት የክለቡ ደጋፊዎች የክለቡን የቦርድ አመራሮች እና የደጋፊ አስተባባሪዎችን በስም በመጥራት ፀያፍ ስድቦችን ይሳደቡ እንደነበር እና በተጨማሪም የስታድየሙን መቀመጫ ወንበር ነቅለው ወደ ሜዳው የመሮጫ ትራክ የወረወሩ በመሆኑም ከዕለቱ የጨዋታ አመራሮች ሪፖርት ቀርቦባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት :-

1. የአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ንብረት የተነቃቀሉ የኘላስቲክ ወንበሮችን ከስታድየሙ አስተዳደር ጋር በመነጋገር እንዲያስጠግኑ
2. በዕለቱ በፀጥታ እና ደህንነት ስራ ላይ የነበሩት የፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ወ/አማኑኤል ተሰማ የፍንከታ ጉዳት የደረሰባቸው እና ሕክምና ማድረጋቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ያወጡትን ወጪ እና የሞራል ካሳ ክለቡ እንዲፈፅም
3. በስታድየሙ ዙሪያ ያለውን የኮሚኒቲ ፖሊስ ቢሮ መስታወት እንዲሁም የስታድየም ዙሪያ ሱቆች መስታወት የተሰበሩ በመሆናቸው ይህንን ከአበበ ቢቂላ ስታዲየም አስተዳደር እና ከአካባቢው ፖሊስ መመሪያ ጋር በመነጋገር እንዲያስጠግኑ ተወስኗል። ስለሆነም ደጋፊዎቹ አፀያፍ ስድብ በመሳደባቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀጽ 66 ተ.ቁ 4 “ሀ” መሰረት 75.000 (ሰባ አምስት ሺህ ብር) እንዲሁም የስታድየሙን መቀመጫ ወንበር ወደ ሜዳው ትራክ በመወርወራቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተራ ቁ 3 “ሀ” መሰረት ብር 25.000 (ሃያ አምስት ሺህ) ብር በድምሩ ክለቡ ብር 100.000 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ እንዲከፍል ተወስኗል። ኢትዮጵያ ቡናም በጉዳዩ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ክለቡ ይፋ አድርጓል።