መረጃዎች | 51ኛ የጨዋታ ቀን

የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ቀጥሎ ይካሄዳል፤ በሁለተኛው የጨዋታ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

ይህንን ጨዋታ ሠለሞን አሸብር በዋና ዳኝነት ሶርሳ ዱጉማ እና ወጋየሁ አየለ በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ

አስራ አራት ነጥቦች ሰብስበው በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው በመውጣት በውድድር ዓመቱ ያስመዘገቡት የአቻ ውጤት ወደ ስምንት ከፍ ያደረጉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በሁለተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ በተከታታይ አስር ሳምንታት ሽንፈት አልቀመሱም። ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ጠጣርና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በመጠኑም የተሻሻለ አቀራረብ ይዘው ጨዋታዎቻቸው በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀድያዎች በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስተናገደና ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አላቸው። በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በታች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸውም በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስተናገደ ቀዳሚ ክለብ ያደርጋቸዋል። ሀድያዎች ምንም እንኳ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መገንባት ቢችሉም በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ ግን እዚ ግባ የሚባል አይደለም።ቡድኑ በአስራ ሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ብቻ አስቆጥሯል፤ ይህ ቁጥርም በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስቆጠሩ ሦስት ክለቦች አንዱ ያደርጋቸዋል። ውስን ለውጦች በማድረግ የቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ያስቀጠሉት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ባለፉት ጨዋታዎች በማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ የታዩት በጎ ጎኖች የማስቀጠል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በተለይም ቡድኑ የሚታይበት ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች የመፍጠር ችግር አንገብጋቢ መፍትሔ ይሻል።

በሀያ ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው የውድድር ዓመቱ አራተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡት ብርቱካናማዎቹ በአስራ አራት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ብርቱካናማዎቹ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ተጫውተዋል። በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የተጋጣምያቸው የመከላከል ክፍተቶች በመጠቀም ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ግቦቹ የተቆጠሩበት መንገድም አንዱ ማሳያ ነው።
ቡድኑ በጨዋታው ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ጨዋታውን ማሸነፉ ተከትሎ ስል የነበረው የማጥቃት ክፍል ትልቅ ውደሳ ተችሮታል፤ ሆኖም በመከላከሉ ረገድ የነበረው ጥንካሬም ቡድኑ ያሳየው ሌላው አወንታዊ ጎን ነበር። ከጣፋጩ ድሉ በፊት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ከሊጉ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ጥምረት ጋር በተደረገ ጨዋታ ግብ ሳያስየናግድ መውጣቱ ሊያስወድሰው ይገባል።

ቡድኑን በጊዝያዊነት የተረከቡት ኮማንደር ሽመልስ አበበ በዋነኝነት ቡድኑ ፈረሰኞቹን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ የታየው የድል ረሀብና ተነሳሽነት የማስቀጠል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። ከዛ በተጨማሪም ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች በአማካይ 2.2 ግቦች አስተናግዶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባካሄዱት ጨዋታ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ላይ በተመሳሳይ ጥሩ ብቃቱን ጠብቆ እንዲሄድ የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ይጠብቃቸዋል።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል ካሌብ በየነ በጉዳት በረከት ወልደዮሐንስ ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። የድሬዳዋ ከተማን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በሊጉ 8 ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተው 3 ጨዋታ ሆሳዕና አሸንፏል። 24 ግቦች በተስተናገዱበት ግንኙነት እኩል 12 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን

የዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት ያላቸው ክለቦች የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል

በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ስር ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በወጣቱ አሰልጣኝ ስር ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አስራ አንዱን አሳክተዋል። ቡናማዎቹ ከአምስት ድል አልባ ጨዋታዎች አገግመው በእንቅስቃሴና በውጤት ረገድ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ቢገኙም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያላቸው ክፍተት ግን እንቅስቃሴያቸው በግቦች እንዳይታጀብ አድርጎታል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠሩም የቡድኑ የማጥቃት ውስንነት ያሳያል።
አሰልጣኙ በነገው ጨዋታ ከመልካም እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑ የፊት መስመር ጥምረት ፍሬአማነት ከፍ የማድረግ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

ሀምበሪቾን ላይ ድል ከተቀዳጁበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ መድኖች ከሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። መድኖች በሊጉ የመጀመርያ ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር ችግር ነበረባቸው፤ በሁለተኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎችም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ነበር። አሁን ግን ምንም እንኳ የቡድኑ ውጤት ላይ ለውጥ ባይመጣም ቡድኑ በአንፃራዊነት በተሻለ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል።
ቡድኑ ከተከታታይ ግብ አልባ ጨዋታዎች በኋላ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማስቆጠሩም የከዚ ቀደም ዋነኛ ችግሩ በመጠኑም መቅረፉ ያሳያል። ሆኖም ወቅታዊው የመከላከል ብቃታቸው የቡድኑ ዋነኛው ችግር ነው፤ ቡድኑ ባለፉት አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስተናገዱ የመከላከል ክፍሉን ድክመት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። መድኖች በነገው ጨዋታ የሚገጥሙት በተመሳሳይ የግብ ማስቆጠር ክፍተት ያለበት ቡድን በመሆኑ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም የኋላ ክፍላቸው ለውጦች እንደሚያስፈልጉት ቁጥሮች ምስክር ናቸው።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ብሩክ በየነና አማኑኤል ዮሐንስ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ በአንፃሩ ጉዳት ላይ የቆየው መሐመድ ኑር ናስር ከጉዳት ተመልሷል። የኢትዮጵያ መድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 27 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 11 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 43 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን 31 ጎሎች አስቆጥሯል።

ተፈሪ አለባቸው በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና አዲሱ የሊጉ ረዳት ዳኛ ደስታ ጉራቻ በረዳትነት ሐይማኖት አዳነ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።