ሪፖርት | አንተነህ ተፈራ ዛሬም ለቡናማዎቹ ሦስት ነጥብን አስገኝቷል

ኢትዮጵያ ቡና ስድስተኛ ድል ፣ ኢትዮጵያ መድን ሰባተኛ ሽንፈት ባገኙበት ጨዋታ ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ ሀትሪክ ታግዘው 3ለ0 አሸንፈዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን ሲረታ ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት የባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ቡናማዎቹ ራምኬል ጀምስን በሬድዋን ናስር ፣ ይታገሱ ታሪኩን በአማኑኤል አድማሱ በመድኖች በኩል ደግሞ አብዱልከሪም መሐመድን በአቡበከር ወንድሙ ፣ ያሬድ ዳርዛን በንጋቱ ገብረሥላሴ ያደረጓቸው ለውጦች ሆነዋል።

ሁለቱን የሊጉ መስራች ክለቦችን ባገናኘው የምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመያዝ በመስመሮች በኩል በጥልቀት ወደ ውስጥ ለመግባት የሚደረግ ጥረትን ተጠቅመው ጫና ለማሳደር ሲዳዱ ከጨዋታው ጅምር አንስቶ ማስተዋል ብንችል ፈጠን ያለ ሙከራን ማድረግ የቻሉት ግን መድኖች ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት አቡበከር ወንድሙ ሲያሻማ መሐመድ አበራ ነፃ ቦታ ሆኖ ያገኘውን በግንባር ገጭቶ በረከት አማረ በጥሩ ቅልጥፍና ይዞበታል። በፈጣን ሽግግር በይበልጥ ሁለቱን ኮሪደሮች ተጠቅመው ቶሎ ቶሎ የተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ላይ ቢጫ ለባሾቹ ሲደርሱ ይታይ እንጂ ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች ለማግኘት ግን አቀራረባቸው ውስንነቶች ይጎሉት ነበር።

ቀጥተኛ አልያም ደግሞ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ቀኝ ባዘነበለ እንቅስቃሴ በጨዋታ መንገዳቸው ሲጠቀሙ የታዩት ኢትዮጵያ መድኖች ይዘውት በገቡት አጨዋወት ልዩነት ለመፍጠር ስኬታማ አልነበሩም። ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች እና ዒላማውን የጠበቀ ሙከራን ቶሎ ቶሎ ለማየት የናፈቀን የቡድኖች ጨዋታ 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ግብ አስመልክቶናል። መስፍን ታፈሠ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ አቀዝቅዞ በአንድ ሁለት ከበፍቃዱ ጋር ተቀባብሎ በፍቃዱ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የላከለትን አንተነህ ተፈራ ከመረብ አዋህዶ ቡናማዎቹን መሪ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል 36ኛው ደቂቃ መስፍን ወደ ግብ መቶ በተከላካይ ተደርባ የመጣችለት ኳስ በፍቃዱ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታ አቡበከር ይዞበታል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተቸግረው የቆዩት መድኖች 38ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረሥላሴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ በረከት አማረ እንደምንም ወደ ውጪ ያዋጣበት የቡድኑ ተጠቃሿ ሙከራ ሆናለች። አጋማሹ ሊገባደድ የመጨረሻዎቹን አምስት ደቂቃዎች ፈጠን ያሉ እንቅስቃሴዎችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያየንበት ቢሆንም በቡና 1ለ0 መሪነት ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መድኖች ወደ ጨወታ ለመመለስ የሚመስልን እንቅስቃሴ በብሩክ አማካኝነት በጊዜ ቢያሳዩንም ከደቂቃ ደቂቃ ግን የኢትዮጵያ ቡና መልሶ ማጥቃት እያየለ የመጣበት ነበር በዚህም ሂደት ቡድኑ ግብ አስቆጥሯል። 47ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ቀኝ የደረሰውን አማኑኤል አድማሱ ወደ ውስጥ የሰጠውን አንተነህ ተፈራ እጅግ አስደናቂ ክህሎት በተሞላበት አጨራረስ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ በመምታት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። ተጨማሪ ጎል ካስተናገዱ በኋላ ወደ ቀኝ መስመር በማጋደል እና የኢትዮጵያ ቡናን ቅብብል በማቋረጥ ሁለት ሙከራዎችን አከታትለው መድኖች አድርገዋል። አሚር ከቀኝ ወደ ውስጥ አመቻችቶ ወገኔ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ያመከናት እና ከአንድ ደቂቃ መልስ ደግሞ ከወንድሜነህ እግር ስር ያሬድ ነጥቆ የሰጠውን ወገኔ ተጫዋች በማለፍ ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን አምክኗታል። መድኖች ወደ ማጥቃት ቀጠናው ሲገቡ ጥለው የሚሄዱበትን ቦታ በፍጥነት ለመጠቀም ተቃራኒ ሜዳ ላይ በቶሎ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች 59ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ግባቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ይታገሱ ታሪኩ ወደ ግራ የሰጠውን መስፍን ታፈሰ ገፋ በማድረግ ወደ ግብ ሲልክለት አንተነህ ተፈራ ሀትሪክ የሰራበትን ግብ በማስቆጠር የቡናን መሪነት ከፍ አድርጓል። የኢትዮጵያ ቡናን ጫና መቋቋም የከበደው የመድን የመከላከል መዋቅር የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ ለማሻሻል ጥረት ቢያደርጉም እምብዛም ውጤታማ መሆን ግን አልቻሉም። ሬድዋን ናስር ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግቡ ቋሚ ከመለሳት አጋጣሚ በኋላ ቡናማዎቹ በአመዛኙ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ኳሱን ለመድን ተጫዋቾች በመልቀቅ ለመንቀሳቀስ ጥረት ያደረጉበት ሂደት ያስተዋልን ቢሆንም መድኖች እንዳገኙት ነፃነት ግን ወደ ጨዋታ ለመግባት ያደረጓቸው ጥረቶች ደካሞች በመሆናቸው ጨዋታው በመጨረሻም በቡና 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቡና ስድስተኛ ድልን መድን በአንፃሩ ሰባተኛ ሽንፈትን በዓመቱ አስመዝግበዋል።


ከጨዋታዉ ፍጻሜ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በሳል ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ አለመኖራቸው እና የታይም ማኔጅመንት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው ተጋጣሚን ለመቆጣጠር አስበው ገብተው ግን በነበረባቸው የኮንሰንትሬሽን ክፍተት አለመሳካቱን ጠቁመው ጨዋታውን የመቆጣጠር ችግር በቡድኑ ውስጥ መኖሩን እና በጨዋታው አጀማመራቸው ጥሩ ቢሆንም ከጎሉ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ መበላሸቱን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብር በበኩላቸው ለእኔ ምርጡ ጨዋታ ነበር ካሉ በኋላ ዕድሎች የተፈጠሩበት የተገኙ ዕድሎችም ወደ ጎልነት የተለወጡበት መሆኑን ተናግረው ከድግግሞሽ በኋላ የተገኘ ውጤት እንደሆነ እና የተሻለ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችም በቡድኑ ውስጥ ስላሉ ይህንን ማስቀጠል ይገባናል በውጤቱም ደስተኛ ነኝ በማለት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።