መረጃዎች | 52ኛ የጨዋታ ቀን

13ኛ ሳምንቱ የሊጉ መርሃግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል የሶስተኛ የጨዋታ ዕለትን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

መቻል ከሲዳማ ቡና

የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር የሊጉን መሪነት ለመረከብ የሚያልሙትን መቻሎችን ከሽንፈት ለመመለስ ከሚያስቡት ሲዳማ ቡናዎች የሚያገናኝ ይሆናል።

በውድድር ዘመኑ አንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት በማስተናገድ እንዲሁም ስምንት ጨዋታዎች በድል የተወጡት መቻሎች አሁን ላይ በሃያ ሰባት ነጥቦች በሰንጠረዡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ ባለፉት አስር መርሃግብሮች ምንሞ ዓይነት ሽንፈት ያላስተናገዱት መቻሎች የነገውን ጨዋታ በድል መወጣት የሚችሉ ከሆነ ነጥባቸውን ወደ ሰላሳ በማሳደግ የሊጉን መሪነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረከብ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር እንደመቻላቸው የነገውን ጨዋታ ከፍ ባለ ትኩረት የሚከውኑት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከአሰልጣኝ ለውጥ በኃላ የተሻለ መነቃቃት ላይ የነበሩት እና ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን ዳግም ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በአስራ አምስት ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተሰይመዋል።

በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ምንም እንኳን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጅርሻ ቢኖራቸውም የኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ግብ ዕድል ለመቀየር የተቸገሩት ሲዳማ ቡናዎች አሁንም ብልጭ ድርግም የሚለውን የቡድኑን የማጥቃት ጨዋታ ይበልጥ ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

በመቻል በኩል ባለፈው ሣምንት በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደው በኃይሉ ግርማ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በሲዳማ ቡና በኩል ቅጣት ላይ የነበረው ጊትጋት ጉት ከቅጣት ሲመለስ ደስታ ደሙ ግን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ይሆናል።

ሁለቱ የነገ ተጋጣሚዎች ከዚህ ቀደም 24 ጊዜ ሲገናኙ ሲዳማ 9 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 8 ጨዋታ አሸንፏል። 7 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 21፣ ሲዳማ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና አማን ሞላ ረዳቶች መለሠ ንጉሴ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ

አስራ ሁለት ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገው መርሃግብር ደግሞ ድል የተራቡትን ባህር ዳር ከተማዎችን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከሳምንታት ጥበቃ በኃላ ከድል ከታረቁት አዳማ ከተማዎች ያገናኛል።

ከፍ ባለ ቅድመ ቅምት የውድድር ዘመኑን የጀመሩት የጣና ሞገዶች ቀስ በቀስ ከዋንጫው ፉክክር እየራቁ ያሉ ይመስላል ፤ ከመጨረሻ አራት የሊጉ መርሃግብሮች ሁለት ነጥብ ብቻ ሲያሳኩ በዚህም በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአስር ነጥቦች ርቀው በስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በብዙ መልኩ የታደከሙ የሚመስሉት የጣና ሞገዶቹ ከሶስት ጨዋታ በኃላ የመጀመሪያ ግባቸውን ከፍፁም ቅጣት ምት ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሲያሳኩ የክፍት ጨዋታ ግብ ፍለጋቸው ግን ሶስት መቶ ስልሳ ደቂቃን ተሻግሯል።

በከፍተኛ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት እፎይታ ያገኙበትን ውጤት በማሳካት የነጥብ ብዛታቸውን ወደ አስራ ስምንት በማሳደግ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ብለው ወደ ዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አምርተዋል።

እንደ ባህር ዳር ከተማ ሁሉ በማጥቃቱ ረገድ ግቦችን ለማግኘት ተቸግረው የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች ባለፈው ሀዋሳ ከተማን ሲረቱ ግን ትንሹ ዮሴፍ ዮሀንስ አዳኛቸው ሆኖ ብቅ ብሏል። በጨዋታው ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ዮሴፍ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ አራት ማሳደግ ሲችል በቀጣይም ቡድኑ ከእሱ አብዝቶ እንዲጠብቅ ያስገድዳል።

ባህርዳር ከተማ አለልኝ አዘነ እና ፍሬዘር ካሳን በአምስት ቢጫ ካርድ ሱሌይማን ትራኦሬን ደግሞ በጉዳት የማያገኙ ሲሆን በአዳማ በኩል አቡበከር ሻሚል ፣ ሀይደር ሸረፋ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ሐቢብ መሐመድ ፣ መላኩ ኤልያስ እና ቻርለስ ሪቫኑ በክፍያ ጥያቄ ምክንያት ከክለቡ ጋር የማይገኙ መሆናቸውን ተከትሎ በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ይመስላል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 8 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር 6 በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አዳማ አንድ አሸንፎ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 9 ሲያስቆጥር አዳማ 1 አስቆጥሯል።

የምሽቱን መርሃግብር በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ ረዳቶች  ለውጥ ሊደረግ በሚችልበት አራተኛ ዳኝነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።