ሪፖርት | መቻል የሊጉን መሪነት ተረክቧል

መቻል ከቆሙ ኳሶች ባገኟቸው ጎሎች ሲዳማ ቡናን 2ለ1 በመርታት የዓመቱ ዘጠነኛ ድላቸውን በማግኘት የሊጉ አናት ላይ ተቀምጠዋል።

ባለፈው ሳምንት መቻል ከፋሲል ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቀበት ጨዋታ በቀይ በወጣው በሀይሉ ግርማ ምትክ ምንተስኖት አዳን ሲተኩ በሀምበሪቾ ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በኩል በተደረገ የአራት ተጫዋች ለውጥ መሐመድ ሙንታሪ ፣ ፂሆን ተስፋዬ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና በዛብህ መለዮ ወጥተው መክብብ ደገፉ ፣ ጊት ጋትኩት ፣ ደግፌ አለሙ እና ዮሴፍ ዮሐንስ ተክተዋቸዋል።

ከረር ባለው የአዳማ ፀሀይ ታጅቦ የጀመረው የቡድኖች ጨዋታ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የኋልዮሽ ቅብብል የበዛበት እንጂ ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች ያላስመለከተን ነበር። መቻሎች ከተከላካይ ክፍል መነሻቸውን በሚያደርጉ ኳሶች መሐል ሜዳውን ከመስመር ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ለመጫወት ሲንቀሳቀሱ ብንመለከትን የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ያደርጉት የነበረው ጥረት ግን ውጤታማ ሲያደርጋቸው አልተስተዋለም። ከፍ ባለ ተነሳሽነት ከኋላ የሜዳው ክፍል ኳስን በማስጀመር አልያም ወደ ግራ ባጋደለ መልኩ እንቅስቃሴያቸውን ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታው ሀያ ደቂቃዎችን እንደተሻገረ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መልኩ ከጎል ጋር ለመገናኘት ቀዳዳ ሲፈልጉ መመልከት ተችሏል።

ሲዳማ ቡናዎች የመቻልን የተከላካይ ክፍል ጫና ውስጥ በሚከት እንቅስቃሴያቸው የሚነጥቋቸውን ኳሶች በቀላሉ ወደ ግብነት መለወጥ የሚያስችላቸውን መልካም አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ቢያገኙም በተለይ ቡልቻ ሹራ ከርቀት ለመሞከር አልያም ደግሞ ከግቡ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ መረጋጋቶች አብረውት አለመኖሩን ተከትሎ ወርቃማ ዕድሎቹን መጠቀም ሳይችላቸው ቀርቷል። እምብዛም ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች ለማየት በእጅጉ ናፍቆን የነበረው ጨዋታ 25ኛው ደቂቃ እንደደረሰ መቻሎች በቀኝ የሜዳው ክፍል ምንይሉ በጥሩ እይታ የሰጠውን ሽመልስ በቀለ ወደ ጎል መቶ መክብብ የመለሰበት እና በድጋሚ ሽመልስ አግኝቶ መረብ ላይ አሳርፏት ከጨዋታ ውጪ የተባለበት አጋጣሚ የተናፈቀችዋ የጨዋታው መልካሟ ሙከራ ሆናለች። 34ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህን በጉዳት አጥተው አቤል ነጋሽን መቻሎች ከተኩ በኋላ በይበልጥ በሲዳማ ቡና ብልጫ ተወስዶባቸዋል።

41ኛው ደቂቃ ከተፈጥሮአዊ ቦታው አማካይ ላይ የተሰለፈው ደስታ ዮሐንስ ከፍቅረየሱስ ጋር በአንድ ሁለት ተቀባብሎ ያገኘውን ኳስ ከግብ ጠባቂው አሊዮዚ ናፊያዝ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ካዳነበት ሙከራ በኋላ አራት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ በቅፅበት የሲዳማ የሜዳ ክፍል መቻሎች ይዘውት የሄዱትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ከግራ ወደ ሳጥኑ ይዞ ለመግባት ሲጥር ጊት ጋትኩት ተጫዋቹ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ምንይሉ ወደ ጎልነት በቀላሉ ቀይሯታል። እንደነበራቸው ብልጫ ጎልን ለማግኘት ከብዷቸው የዋሉት ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ጭማሪ ላይ በምንይሉ ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም መክብብ አምክኗት በ1ለ0 ውጤት ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሲዳማ ቡናዎች የተጫዋች ለውጥን አድርገው ተመልሰዋል። ደግፌ አለሙ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን በይገዙ ቦጋለ እና በዛብህ መለዮን በመተካት ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በሽግግር የጨዋታ መንገድ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ማድረግን ከአጋማሹ መጀመር አንስቶ ሲተገብሩ ተመልክተናል። በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው በተጫዋቾቻቸውን ላይ የሚሰራባቸውን ጥፋት መነሻ አድርገው ከቆሙ ኳሶች ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር ቀላል የማይባሉ ዕድሎችን ያገኙት መቻሎች 59ኛው ደቂቃ ላይ ተጋጣሚያቸው እንደነበረው ብልጫ ጎል አስቆጥሮባቸዋል። በረጅሙ ወደ ግራ የተጣለን ኳስ ወደ ሳጥን ይገዙ ይዞ ሊገባ ሲል አስቻለው ጥፋት በተጫዋቹ ላይ መፈፀሙን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ይገዙ ሲመታ የግቡ ቋሚ ብረትን ገጭቶ ኳሱ ሲመለስ በዛብህ ደርሶት ከግራ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ቡልቻ በግንባር ጨረፍ ያደረጋትን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በራሱ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል።

ከኳስ ጋር በምቹነት ሳይቸገሩ የተቃራኒ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በቀላሉ ሲዳማ ቡናዎች መድረስ ቢችሉም ከወገብ በታች ያሉ ተጫዋቾቻቸው በተደጋጋሚ የሚሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የሚገኙ የቅጣት ምት ኳሶች መቻሎችን ወደ መሪነት እንዲመጡ አስችሏቸዋል። 72ኛው ደቂቃ ከግራ የሜዳው ጠርዝ ወደ መስመር ከተጠጋ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት ሽመልስ በቀለ ሲያሻማ ተቀይሮ የገባው አበባየሁ ዮሐንስ በግንባር ጨርፎ በራሱ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። የጨዋታው የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉከክርን ብናይበትም 86ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትኩት ለመክብብ ኳስን ወደ ኋላ ለማቀበል ሲል ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ የግቡን አግዳሚ ብረት ገጭታ የወጣችበት ምናልባትም የመቻልን መሪነት የምታሰፋ አጋጣሚ ነበረች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ላይ ዮሴፍ ለሲዳማ ከርቀት አክርሮ መቶ አሊዮዚ ካዳነበት ሙከራ መልስ በመጨረሻም በ2ለ1 የጦሩ አሸናፊነት ተቋጭቷል። መቻል ዘጠኛ ድሉን በማሳካት የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና ስድስተኛ ሽንፈታቸውን በጨዋታው አስተናግደዋል።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሁለቱም አጋማሾች የተለያዩ እንደነበሩ ጠቁመው በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ዕድልን አግኝተው አለመጠቀም መቻላቸው የተከላካይ ተጫዋቾች ላይ ጫና እንዳሳደረ እና ከዕረፍት በኋላ ግን ቅያሪዎችን በማድረግ ለማስተካከል ሞክረው አለመሳካቱን እና በፍፁም ዕድለኛ እንዳልነበሩም ጭምር ተናግረዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ተጫዋቾች ላይ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ስለነበረባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር ጠቁመው ተጫዋቾቻቸው ላይ ነፃነት እንዳለ ግን ትልቁ የቡድናችን ችግር ፖዚሽን መሆኑን ጠቁመው ይሄንንም እናስተካክላለን ያሉ ሲሆን በቡድናቸው ውስጥ ግን አልሸነፍ ባይነት መኖሩን ጠቁመዋል።