ሪፖርት | ሀምበርቾ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ምሽት ላይ የተደረገው የሀምበርቾ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለ ግብ ተቋጭቷል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ትግሎት ባሻገር የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር። ሆኖም የአጋማሹ የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ በሀምበርቾዎች አማካኝነት ሲደረግ አፍቅሮተ ሰለሞን በሳጥኑ የግራ ጠርዝ ዋሳዋ ጄኦፍሪ እና ሬድዋን ናስርን በግሩም ክህሎት አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አስወጥቶበታል።


ከራሳቸው የግብ ክልል በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ 16ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አንተነህ ተፈራ ከዋሳዋ ጄኦፍሪ ከቅጣት ምት በተሻገረላቸው ኳስ በግንባር ገጭተው ካደረጉት ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ እና ያልተደረጁ ቅብብሎች ጨዋታው ይበልጥ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ቡናማዎቹ ከበርካታ ጨዋታዎች በኋላ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ሀምበርቾዎች የተሳካ የመከላከል ጊዜ ለማሳለፍ ሲታትሩ ተስተውሏል። ሆኖም አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል አጋማሹ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ በሀምበርቾ በኩል ማናየ ፋንቱ በቡና በኩል ደግሞ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ በጥሩ እንቅስቃሴ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ዒላማውን የጠበቀ አልነበረም። ሆኖም የተሻለው የግብ ዕድል 51ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና አማካኝነት ሲፈጠር በፍቃዱ ዓለማየሁ በግሩም ሩጫ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ የቀነሰውን ኳስ አንተነህ ተፈራ ሙሉ በሙሉ ሳያገኘው ቀርቶ አባክኖታል። አንተነህ ኳሱን እንደፈለገው እንዳይጠቀምበትም የሀምበርቾው ተከላካይ ታየ ወርቁ ንክኪ ሚናው ትልቅ ነበር።


ሀምበርቾዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ጥቅጥቅ ብለው መከላከልን በመምረጥ ለተጋጣሚያቸው ፈታኝ ሆነው ሲቀጥሉ ቡናማዎቹ በአንጻሩ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በሚያገኙት ኳስ ሁሉ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በቀሪ ደቂቃዎችም ሀምበርቾዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት ሰዓት መግደልን በመምረጣታቸው በየ ደቂቃው የሚቆመው ጨዋታ አሰልቺ እየሆነ ሲቀጥል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሀምበርቾ በኩል በረከት ወንድሙ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ አብዱልከሪም ወርቁ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ መላኩ ከበደ የቡናን በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ እንደገቱ በመግለጽ ከተደጋጋሚ ሽንፈት ከመምጣታቸው አንጻር አንድ ነጥብ ለማግኘት መፈለጋቸውን እና ያንንም እንዳሳኩ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ በበኩላቸው ተጫዋቾች የሚችሉትን ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩልም ሆነ በእንቅስቃሴው በኩል መዳከማቸውን ሲገልጹ ሆኖም ግን አንዱ ነጥብ በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።