መረጃዎች| 59ኛ የጨዋታ ቀን

የሳምንቱ ሁለት ትላልቅ መርሀ-ግብሮች የሚስተናገድበት የጨዋታ ቀን የተመለከቱ መረጃዎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

ፈረሰኞች ወደ ድል ለመመለስ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ አሸናፊነታቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ሀያ አምስት ነጥቦች ሰብስበው ከመሪው በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሦስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ድል፣ ሦስት አቻና ሁለት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል፤ ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት ማግኘት ከሚገባው ሀያ አራት ነጥቦች ግማሹን አሳክቷል። ቁጥሮቹ እንደሚያመላክቱት ፈረሰኞቹ የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል፤ ከዚ በተጨማሪም ቡድኑ በስምንት ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ ጨዋታዎች አለማሸነፉ ለወጥነት ችግሩ ሌላ ማሳያ ነው።
ፈረሰኜቹ በተጠቀሱት የቅርብ ሳምንታት ጨዋታዎችም ስድስት ግቦች አስተናግደው ዘጠኝ ግቦች ቢያስቆጥሩም በፊት መስመራቸው ላይ የአፈፃፀም ችግር ይታያል። ከወላይታ ድቻ ጋር ባካሄዱትና በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በነበራቸው ጨዋታ ላይ ቡድኑ ሁነኛ የፊት መስመር ተጫዋች ክፍተት እንዳለበት ያመላከተ ነበር። ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ የማጥቃት ክፍላቸው ላይ በቂ አማራጭ እንደሌለ የገለፁት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በነገው ዕለትም ተመሳሳይ የተጫዋቾች ምርጫ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።

ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ንግድ ባንክን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች የድል መንገዳቸውን ለማስቀጠል ቅዱስ ጊዮርጊስን ይገጥማሉ። ሲዳማዎች ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በፊት ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ድልና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ሊጉ አናት መጠጋት ቢችሉም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በገጠማቸው ሽንፈት የድል መንገዳቸው ተገቶ ነበር። በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ ግን በሰንጠረዡ አናት ካሉት ቡድኖች አንዱ የሆነው ንግድ ባንክ አሸንፈው ዳግም ወደ ድል ተመልሰዋል። ሲዳማዎች ባለፉት ሳምንታት በሊጉ ሰንጠረዥ ከነሱ በላይ የተቀመጡትን ንግድ ባንክ፣ ባህርዳር ከተማና ወላይታ ድቻ አሸንፈው እንደመምጣታቸው በነገው ጨዋታ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ሆኖም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ አስተናግዶ በጥሩ ብቃት ላይ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስተናግዷል፤ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የተቀዛቀዘውን የተከላካይ ክፍላቸው የመጠናከር ስራ ይጠብቃቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከታዳጊዎቹ ሀሮን አይተን እና ሀፍቶም ገብረ እግዚአብሄር በስተቀር ሁሉም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በሲዳማ ቡናዎችም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም፤ ከጉዳት የተመለሰው ደስታ ደሙ በዚ ጨዋታ የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 26 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 37 ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ሄኖክ አበበ በዋና ዳኝነት፤ ወጋየሁ አየለ እና ዘመኑ ሲሳዬነው ረዳቶች መለሠ ንጉሴ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በሀያ ሦስት ነጥቦች አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ወደ መሪዎቹ የሚጠጉበት ነጥብ ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ዐፄዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈት ካስተናገዱበት ስምንተኛው ሳምንት በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ምርጥ የተከላካይ ክፍል አላቸው። በሊጉም ከሀድያ ሆሳዕና ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስተናገደ ክለብ ነው። ሆኖም በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ክፍተት የቡድኑ ዋነኛ ችግር ነው። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ድርሻ ተሽሎ በታየባቸው ጨዋታዎች ላይ የነበረው ዕድሎች የመጠቀም ችግር መቅረፍ ይኖርበታል። በርግጥ ቡድኑ በተጠቀሱት ስድስት የቅርብ ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ሰባት ግቦች አስቆጥሯል፤ ሆኖም ኳስቆጠራቸው ሰባት ግቦች አምስቱ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ የተመዘገቡ ናቸው። በተቀሩት አራት ጨዋታዎች ማስመዝገብ የቻሉት የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው። ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ላይ የግብ ዕድሎች የመጠቀም ችግር እንዳለባቸው የጠቀሱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ውስን ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አስተናግደው ከመሪነታቸው የወረዱት ንግድ ባንኮች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ፋሲል ከነማን ይገጥማሉ። ንግድ ባንኮች ከዚ ቀደም የነበረው ጨዋታ የመቆጣጠር ዋነኛ ጥንካሬያቸው ማስቀጠል አልቻሉም፤ ይህ ችግርም በቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ሽንፈት በገጠማቸው ተከታታይ ጨዋታዎች በጉልህ ታይቷል፤ በነገው ጨዋታም የአማካይ ክፍል ብልጫ ወስዶ ጨዋታዎች ለመቆጣጠር የማይሰንፈውን ፋሲል ከነማን እንደመግጠማቸው በርካታ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከዚ በተጨማሪ ቡድኑ በተከታታይ የማሸነፍ መንገድ በነበረበት ወቅት ግሩም የነበረውና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አምስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው በአሰልጣኝ በፀሎት ለውጥ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሌላው ክፍል ነው።

በዐፄዎቹ በኩም ሚኬል ሳማኬ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ፍቃዱ ዓለሙ በጉዳት ጨዋታቸው እንደሚያመልጣቸው የተረጋገጠ ሲሆን የምኞት ደበበ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

በንግድ ባንክ በኩል ብሩክ እንዳለ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ለነገው ጨዋታ አይደርስም፤ ሆኖም ሱሌማን ሐሚድ እና ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ቅጣታቸውን ጨርሰው ቡድናቸውን ለማገልገል የሚመለሱ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በሦስት አጋጣሚዎች ተገናኝተው ባንክ 2 ድል ሲያስመዘግብ ፋሲል አንዱን አሸንፏል። ባንክ 5፣ ፋሲል 2 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።

ጨዋታው በባህሩ ተካ የመሀል ዳኝነት ይመራል። በረዳትነት ደግሞ ሲራጅ ኑርበገን እና ሙሉነህ በዳዳ፤ አራተኛ ዳኛ መስፍን ዳኜ ሆኖ ተሰይሟል።