ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ድል ተመልሷል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በአማኑኤል ተርፉ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን 1ለ0 ረተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ ፈረሰኞቹ ከወላይታ ድቻ ጋር 1-1 ሲለያዩ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል። ሲዳማዎች በአንጻሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መክብብ ደገፉ ፣ ደግፌ ዓለሙ ፣ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን እና አቤኔዘር አስፋው ወጥተው በምትካቸው መሐመድ ሙንታሪ ፣ በዛብህ መለዮ ፣ ቡልቻ ሹራ እና ማይክል ኪፖሩል ተተክተዋል።


09፡00 ላይ በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ የፊሽካ ድምፅ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል ሲዳማዎች መጠነኛ ብልጫን ወስደዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ 11ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማዎች አማካኝነት ተደርጎም ብርሃኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ ብርሃኑ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ ጊት ጋትኮች በግንባር ገጭቶት ለጥቂት ወጥቶበታል።

በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተዳክመው የቀረቡት ፈረሰኞቹ የአጋማሹን ብቸኛ የግብ ዕድል 20ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ረመዳን የሱፍ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ሞሰስ ኦዶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀሪ 25 ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል አማኑኤል ኤርቦን በተገኑ ተሾመ ቀይረው በማስገባት እና በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ግሩም አጀማመር ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 53ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሄኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ በግሩም ሁኔታ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ሲዳማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የጨዋታ ግለታቸውን በመጠኑ ማነቃቃት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ፈታኝ ሆነው መቅረብ አልቻሉም። ይባስ ብሎም 66ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። ዳግማዊ አርዓያ ከናትናኤል ዘለቀ በተሻገረለት ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ በጥሩ ብቃት አስወጥቶበታል።

የጠሩ የግብ ዕድሎች አይፈጠሩ እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ በሲዳማ በኩል 69ኛው ደቂቃ ላይ ይስሃቅ ካኖ መሬት ለመሬት መትቶት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በቀላሉ የያዘበት ኳስ የተሻለው ሙከራቸው የነበር ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል 81ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ በግሩም ሩጫ እየገፋ በግራ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው አማኑኤል ኤርቦ ኳሱን ሳያገኘው ቀርቶ አባክኖታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፉክክሩ በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ በሲዳማ ቡና በኩል ደስታ ዮሐንስ 90+1ኛው ደቂቃ ላይ በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ አማኑኤል ኤርቦ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ካደረጉት ሙከራ ውጪ የተለየ ፈታኝ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ሳይደረግ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ግብ ያስተናገዱበት መንገድ እንዳናደዳቸው ገልጸው ተጫዋቾቹ ላይ የተናገሩትን የጨዋታ መንገድ የመቀበል ችግር እንዳዩ አበክረው ገልጸዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጎሉን ያስቆጠሩት በሚፈልጉት መንገድ መሆኑን ጠቁመው ዕረፍት ላይ ታክቲካል ነገሮችን አስተካክለው እንደቀረቡ በተጫዋቾችም እንደኮሩ ሲናገሩ የአጥቂ ቦታ ላይ ተጫዋች ማስፈረም እንደሚፈልጉ ሀሳባቸውን ስጥተዋል።