ሪፖርት | የሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል

ለተመልካች ሳቢ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ፋሲል ከነማን 4ለ2 ረቷል።

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ ዐፄዎቹ በ14ኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 1ለ1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ዮናታን ፍስሃ በሚኬል ሳማኬ ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ዓለምብርሃን ይግዛው ተተክተው ሲገቡ ባንኮቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት በሲዳማ ቡና 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ፍሬው ጌታሁን ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ኤፍሬም ታምራት በፓላክ ቾል ፣ ገናናው ረጋሳ እና ተስፋዬ ታምራት ተተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።


ምሽት 12 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ግሩም አጀማመር ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ይሁን እንዳሻው ከመሃል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ የተቆጣጠረው ጌታነህ ከበደ ወደ ኋላ በመምታት ለአማኑኤል ገብረሚካኤል አመቻችቶ ሲያቀብለው አማኑኤልም ሱሌይማን ሀሚድን አታልሎ በማለፍ በግሩም አጨራረስ ኳሱን በግራ እግሩ መሬት ለመሬት በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ከበርካታ ጥረቶች በኋላ 27ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አዲስ ግደይ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በግቡ የግራ የላይኛው ክፍል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 32ኛው ደቂቃ ላይ የዐፄዎቹ አማካይ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ ያደረገው በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ኳስ ተጠቃሽ የማጥቃት ሙከራ ነበር። ሆኖም በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ፋሲሎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል ዮናታን ፍስሃ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ሽመክት ጉግሳ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮታል።

ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ለተመልካች ሳቢ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 42ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ወደ አቻነት ተመልሰዋል። ኤፍሬም ታምራት በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ውስጥ ሲያሻግረው የግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ካሌብ አማንክዋህ በግንባር ገጭቶ ግብ አድርጎታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ቢኒያም ጌታቸውን በአቤል ማሙሽ ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን ያጠናከሩት ንግድ ባንኮች 51ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ጥፋት ተሠርቷል በሚል ሲሻርባቸው 55ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ለማቀበል ሲሞክር በሠራው ትልቅ ስህተት ኳሱን ለኪቲካ ጅማ ሲያቀብለው ኳሱን ያገኘው ኪቲካም ተቀይሮ ለገባው ቢኒያም ጌታቸው አመቻችቶለት ቢኒያም በቀላሉ አስቆጥሮታል።

በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ዐፄዎቹ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በዮናታን ፍስሃ ቀይረው በማስገባት በመጠኑ ለማነቃቃት ቢጥሩም 69ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንዳሻው ከኤልያስ ማሞ በተመቻቸለት ኳስ ከረጅም ርቀት ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የተጋጣሚን ሳጥን ለመፈተን ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 73ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከጌታነህ ከበደ በተሻገረለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፋሲሎች ባላቸው የማጥቃት ኃይል ሁሉ ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ ተስተውሏል። ሆኖም እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 7 ደቂቃዎች ውስጥ 3ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ታዳጊው ዳዊት ዮሐንስ በገባበት ቅጽበት ቢኒያም ጌታቸው ከመናፍ ዐወል ጋር ታግሎ ያመቻቸለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ማራኪ በሆነ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ እንደነበራቸው ጠቁመው ሙሉ ለሙሉ ተጭነው ለመጫወት መሞከራቸውን በመግለጽ ጨዋታውን የማሸነፍ ዕድል እንደነበራቸው እና በጥቃቅን ስህተት እንደተሸነፉ ሲገልጹ በየጨዋታው ሙሉ የተጫዋች ስብስብ አለማግኘታቸው የመጀመሪያውን ዙር ውድድር እንዳከበደባቸው ሀሳባቸውን ሲሰጡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ክፍት የሆነ እና ጥሩ ሽግግር የታየበት ጨዋታ እንደነበር እና የተቆጠሩባቸው ግቦች በቀላሉ እንደተቆጠሩ በመናገር ከዕረፍት መልስ የቡድን ሥራቸውን ለማስተካከል ተነጋግረው ያም እንደተሳካላቸው ገልጸዋል።