የኢትዮጵያ ዋንጫ | ኢትዮጵያ ቡና በአሳማኝ ብቃት ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል

በዛሬው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ መርሃግብር ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ሌላኛው ቡድን መሆኑን አረጋግጧል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በቅርቡ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀና ለሚጠበቀው የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው የሽኝት መርሃግብር እና ስጦታዎችን በማበርከት የጀመረው ተጠባቂው ጨዋታ በግብ ሙከራዎች ረገድ እጅጉን ቀዝቃዛ የነበረ ሲሆን በአጋማሹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር ሆነ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

በ8ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዩሀንስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረው እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ ያደረጉት ሙከራ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች በ32ኛው ደቂቃ የሚገባቸውን የመሪነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በፋሲል ሳጥን ውስጥ በነፃነት ኳሷን ያገኘው መሀመድኑር ናስር ተረጋግቶ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ አስገኝቷል።

በብዙ መመዘኛዎች ደካማ የነበሩት ፋሲሎች በቡና የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ በማለም ገና አጋማሹ ሳይጠናቀቅ ጋቶች ፖኖምን በናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በተመካት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በመጠኑም ቢሆን አጋማሹን በተሻለ መነቃቃት መቋጨት ችለዋል ፤ በዚህም ምንም እንኳን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም በተሻለ ለኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ቀርበው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።

በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በአጋማሹ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር የቻለው መሀመድኑር ናስር ባጋጠመው ጉዳት መነሻነት በአማኑኤል አድማሱ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም በ47ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ያሳደጉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በፋሲል ተከላካዮች ስህተት የተገኘችውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ በሚካኤል ሳሚኪ አናት ላይ በማሳለፍ ማስቆጠር ችሏል።

በ54ኛው ደቂቃ በፋሲል ከነማዎች በኩል የጨዋታው የመጀመሪያ በነበረው ዒላማውን በጠበቀ ሙከራቸው ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጭ እጅግ አስገራሚ ሙከራን ቢያደርግም በረከት አማረ በግሩም ሁኔታ ሊይዝበት ችሏል ፤ በአጋማሹም ፋሲሎች አምብዛም የሻለ ነገር ሜዳ ላይ ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር።

በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች አደጋ ለመፍጠር ሲቃጡ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ65ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከገባ በኃላ ምርጥ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው አማኑኤል አድማሱ በግሩም ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ የሰጠውን ኳስ ተጠቅሞ መስፍን ታፈሰ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን ሶስተኛ ግብ አስቆጥሯል።

በ74ኛው ደቂቃ ላለፉት ዓመታት በዐፄዎቹ ቤት ድንቅ ጊዜያትን ያሳለፈው ሱራፌል ዳኛቸው ተቀይሮ ሲወጣ በስታዲየሙ ከታደሙ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ደመቅ ባለ ሞራል ተሸኝቷል።

በ82ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ዓለማየሁ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስን መስፍን ታፈሰ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ የቡድኑን ማሳረጊያ ግብ ሲያስገኝ በደቂቃዎች ልዩነት ፋሲል ከነማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ ቡድን ከባዶ መሸነፍ የታደገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናዎች የ4-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ በግማሽ ፍፃሜው የሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማን አሸናፊ የሚገጥም ይሆናል።