የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ልደታ ክ/ከ እና መቻል ድል አርገዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ሁለቱ በመሸናነፍ ሲጠናቀቅ አንዱ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጠዋታ አራት ሰዓት ስል የጀመረው ጨዋታ ሀምበርቾን ከልደታ ክ/ከተማ አገናኝቶ ልደታዎች ባለቀ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ድል አድርገዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው በ4 ሰዓቱ ጨዋታ ልደታ ክ/ከተማ የመጀመሪያዎቹን ሰላሳ ደቂቃ ከተጋጣሚው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማድረግ ሲችል ሀምበርቾ በአንፃሩ ደካማ የሚባል የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል።

በኳስ ተሽለው የተገኙት ልደታዎች በ11ኛው ደቂቃ ማናየሽ ተስፋዬ ከርቀት መጥታ ባስቆጠረችው ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ብዙም የግብ ሙከራዎች ባልታየበት በዚህ ጨዋታ ሀምበርቾዎች አልፈው አልፈው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ለማየት ተችሏል። በ38ኛው ደቂቃ ብርሃን ኃይለሥላሴ ከመሃል ሜዳ አከባቢ አክርራ መጥታ ግብ አስቆጥራ አቻ ሆነው ወደመልበሻ ክፍል እንዲመለሱ አድርጋለች።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሁለቱም ቡድኖች ደካማ የሚባል የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም የግብ ሙከራ አድርገዋል። ሀምበርቾዎች የመከላከል ስልት ሲጠቀሙ ተስተውለዋል። ልደታዎች በአንፃራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ቢያድርጉም ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እምብዛም የግብ ሙከራ ሳይታይ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ውስጥ የሀምበርቺ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ልደታ ክ/ከተማ አግኝተዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን ትመር ጠንክር 90+4 ደቂቃ ላይ ከመረብ ጋር አገናኝታ ልደታዎች ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችላለች።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ የጀመረው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን ከመቻል አገናኝቶ መቻሎች ከፍፁም ጨዋታ በላይነት ጋር ማሸነፍ ችለዋል።

ገና ጨዋታው እንደጀመረ የግብ ሙከራዎች መታየት በጀመሩበት በዚህ ጨዋታ መቻሎች ተጋጣሚያቸው ላይ የኳስ ብልጫ ወሰደው ኳስን ወደፊት ሲያንሸራሽሩ ለመመለከት ተችሏል። ጨዋታው በጀመረ ገና በ6ኛው ደቂቃ የመቻሎቹ አምበል የሆነችዋ ቤተልሔም በቀለ ከተከላካይነት መስመር በመሄድ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ መቻሎችን መሪ አድርጋለች።

ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመነቃቃት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጠንከራውን የመቻል የተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ለማስቆጠር ተስኗቸዋል ። እንዲሁም መቻሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ግን በመጀመሪያ አጋማሽ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በመቻል 1ለ0 መሪነት ዕረፍት መውጣት ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ጠንከር ብለው የገቡት መቻሎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ነበሩ። በ54ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ታደለች አብርሃም ከመረብ ጋር አገናኝታ መሪነታቸውን ወደሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ይርጋጨፌ ቡናዎች ደካማ  እንቅሰቃሴ ያስመለከቱበትን ሁለተኛ አጋማሽ ሲያሳልፋ በተለይም ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲከላከሉ ለመመለከት ተችሏል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ውስጥ በ90+4 ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ስንታየሁ ኤርኮ በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ በመግባት ከመረብ ጋር አገናኝታ መቻል ሦስት ነጥብ ከሦስት ግብ ጋር እንዲጎናጸፍ አድርጋለች። በዚህም ጨዋታው 3ለ0 በሆነ ውጤት በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዕለቱ ማሳረጊያ መርሃግብር ሲዳማ ቡናን ከአርባምንጭ ከተማ አገናኝቶ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ጥሩ ፉክክር ባሳየው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራ ለተመልካች አስመልክተዋል። አርባምንጭ ከተማ አሸንፈው ነጥባቸውን ከፍ በማድረግ ወደመሪዎቹ ለመጠጋት በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ጥረታቸው ሊሳካላቸው አልቻለም።

ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ከጠንካራው አርባምንጭ ከተማ ነጥብ ለመጋራት ወደኋላ አፈግፍገው የተጫወቱ ሲሆን አለፈው አለፈውም ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን እንዲሁም አስቆጪ የሚባሉ ኳሶችን አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ብዙ የግብ ሙከራዎች ቢያደርጉም ግብ ሳይቆጠር ወደመልበሻ ክፍል ለመመለሰ ተገደዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገቡት አዞዎቹ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ለግብ የተቃረቡ የኳስ ዕድሎችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

አርባምንጮች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው ቢገቡም ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የሲዳማ ቡና ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ለማስቆጠር ተስኗቸዋል። በዚህም ጨዋታው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።